ቀጥታ፡

የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል -የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል በሰላም እንዲከበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አጠናቆ ወደ ተግባር መግባቱን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረሃይል አስታወቀ፡፡

ለእምነቱ ተከታዮችም በዓሉ የሰላምና የደስታ እንዲሆንላቸው ግብረ ኃይሉ መልካም ምኞቱን ገልጿል፡፡

የቅድመ ዝግጅት ስራውን አስመልክቶም የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው የመሩት ውይይት ተካሒዷል።

በውይይቱም ህብረተሰቡና የፀጥታ ኃይሉ በቅንጅት በመስራታቸው ከዚህ ቀደም ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ልዩ ልዩ በዓላት በሰላም እንደተከበሩት ሁሉ አሁንም የህዝቡን አቅም በተገቢው መጠቀም እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

1445ኛው የኢድ አል አድሃ (አረፋ) በዓል ምክንያት በማድረግም በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በዙሪያው እንዲሁም በአቃቂ ቃሊቲ፣አና በሌሎች ክፍለ ከተሞቾ ላይ በሚገኙ መስጂዶች ለሚከናወነው የኢድ ሶላት ስነ-ስርዓት የፀጥታ አካላት ለሚያከናውኑት የፀጥታ ስራ ምዕመናኑ ተባባሪ እንዲሆን ግብረ -ሐይሉ ጠይቋል።


 

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ በሰጡት የስራ መመሪያ ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት የሚያከብራቸው በዓላት ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

የሀገራችን ሰላም መሆን እንቅልፍ የሚነሳቸውንና በህብረተሰቡ ውስጥ ተመሳስለው የሚገኙትን ፀረ-ሰላም ኃይሎች የመመንጠሩ ስራ እንዲሁም በዘረፋ፣ በሌብነት እና በሌሎች ወንጀሎች ላይ የተሰማሩ ህገ-ወጦች ላይ የተጀመረው ኦፕሬሽን ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ ሊዲያ ግርማ በበኩላቸው መላው የከተማችን ነዋሪዎች የፀጥታውን ስራ በመደገፍ በኩል እያበረከቱት ያለውን አስተዋፅኦ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

አክለውም የሰላም ሰራዊት አባላት ለከተማችን ሰላም እየተወጡት ያለውን ድርሻ በማጎልበት ለበዓሉ ሰላማዊነት ከፀጥታ አካሉ ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ አቅጣጫ ተሰጥቷል ብለዋል፡፡

በያዝነው ዓመት በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ልዩ አለም አቀፍ እና አህጉራዊ ፕሮግራሞች እንዲሁም ህዝብ በስፋት ወደ አደባባይ በመውጣት ያከበራቸው ኃይማኖታዊ ፣ብሔራዊ በአላት ካለምንም የፀጥታ ችግር መከበራቸውን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አስታውሰዋል፡፡

የእነዚህ ኩነቶች በሰላም መጠናቀቅ ዋነኛው ምክንያት የፀጥታ ኃይሉ ከሰላም ወዳዱ ህብረተሰብ ጋር ተቀናጅቶ መሆኑንም አስረድተዋል።

በአዲስ አበባ ስታዲዮምና በልዩ ልዩ መስጂዶች ከሚደረገው የሶላት ስነ-ስርዓት በተጨማሪ በተለያዩ በክፍለ ከተሞች ለሚከናወነው የኢድ ሶላት የሚመጡ ምዕመናን ለጋራ ደህንነት ሲባል ፍተሻ ስለሚኖር ህብረተሰቡ ይህንን ተገንዝቦ የተለመደ ትብብሩ እንዲያደርግ የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡

ለስራው ስኬታማነት ህብረተሰቡ እያደረገ ላለው ትብብር ግብረ ኃይሉ ምስጋናውን አቅርቦ ጥቆማ ለመስጠትም ይሁን የፖሊስን አገልግሎት ለማግኘት በስልክ ቁጥር 011-5-52-63-03 እና 011-5-52-40-77 መጠቀም እንደሚቻል ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም