ቀጥታ፡

ለወባ በሽታ መስፋፋት መንስኤዎችን ለመከላከል  ይሰራል -ጤና ሚንስቴር

ሚዛን አማን፤ ሰኔ 7/2016 (ኢዜአ)፦ ለወባ በሽታ መስፋፋት መንሰኤዎችን  ለመከላከል እንደሚሰራ የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።  

የወባ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታት ያለመ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።

የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ ላይ እንዳሉት ከ75 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ መልክዓ ምድር ለወባ በሽታ መስፋፋት አመቺ ነው።

በአንዳንድ የሀገሪቱ አካባቢዎች የወባ ስርጭት መጠን ከጊዜ ወደጊዜ እያደገ በመሆኑ የወባ መከላከል ሥራውን በልዩ ትኩረት ማከናወን ይገባል ብለዋል።

የወባ በሽታ ጠፍቷል የሚል አስተሳሰብ፣ የመከላከያ መንገዶችን በአግባቡ አለመተግበር እና የጤና ኤክስቴንሽ ፕሮግራም ተጠናክሮ አለመቀጠል የወባ በሽታ እንዲስፋፋ ካደረጉ ምክንያቶች መካከል መሆናቸውን ዶክተር ደረጀ ገልጸዋል።

"በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለይቶ መፍታት ቀዳሚ አጀንዳ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ወባ የሚያስከትለውን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ለማስቀረት ሕዝብን ያሳተፈ ሥራ ይሰራል ብለዋል።

በህብረተሰቡ ተሳትፎ የሚከናወኑ ሥራዎች የወባ ስርጭትን ለማስቆም የጎላ ሚና እንደሚኖራቸውም ዶክተር ደረጀ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢኒስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ኃይሉ በበኩላቸው የበሽታው አምጪ ተዋህስያን ባህሪ መቀያየርና መድኃኒት መላመድ የመከላከል ሥራውን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

ይህንን መሠረት በማድረግ ኢኒስቲትዩቱ የጥናትና ምርምር ሥራዎችን ጨምሮ ሁሉን አቀፍ የወባ መከላከል ሥራዎች እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የበሽታው ስርጭት በስፋት እንደሚታይ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ ናቸው። 

 

በሽታውን ለመከላከል በተሠሩ ሥራዎች የተወሰኑ ውጤቶች ቢገኙም አሁንም ጫናው እንዳልቀነሰ ገልጸዋል።

የወባ ስርጭትን ለመግታት የክልሉ መንግስት ተጨማሪ በጀት ከመመደብ ባለፈ ወባን መከላከል ቀዳሚ አጀንዳ አድርጎ ይሠራል ብለዋል።

የወባ በሽታ መከላከል ሥራው እስከ ቀበሌ ድረስ በተደራጀ መልኩ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ናቸው።


 

ወባን መከላከል የክረምት ወራት የወጣቶች በጎ ፈቃድ አገልግሎት አንዱ ዘርፍ ሆኖ እንዲሠራ አቅጣጫ ተቀምጦ ወደ ተግባር መገባቱንም ጠቁመዋል።

በሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ የፌዴራል እና የክልሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

     

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም