ቀጥታ፡

የግብርናውን ዘርፍ ምርታማነት ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016 (ኢዜአ)፦ የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በዘርፉ የተሰማሩ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ተመላከተ።   

በግብርና ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ልማት ባንክ ትብብር በግብርና ኢንቨስትመንት ተግዳሮቶችና ቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ያተኮረ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

በመድረኩ የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም በዘርፉ የተሰማሩ ግለሰቦች ታድመዋል።

በውይይቱ ዘርፉን በቴክኖሎጂ በመሰረተ ልማት መደገፍ እንደሚገባና የግንኙነት አግባቦች ማደግ እንዳለባቸው ተመላክቷል። 

ለሚያጋጥሙ ችግሮችም በየወቅቱ መፍትሄ እየሰጡ መሄድ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊ የሥራ ኃላፊዎች ግብርና የተለያዩ ዘርፎችን የሚነካ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ከተለያዩ ተቋማት ጋር ተቀራርበው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዝዳንት ዮሃንስ አያሌው(ዶ/ር) በበኩላቸው ባንኩ ለግብርና ልማት ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት ለግብርና ፕሮጀክቶች የወለድ ምጣኔ ከ 11 ነጥብ 5 በመቶ ወደ 7 በመቶ ዝቅ ማድረጉን ገልጸዋል።


 

እንዲሁም የግብርና ሜካናይዜሽንን በትኩረት እየደገፈ መሆኑን አመላክተዋል።

በ2015 በጀት ዓመት በሊዝ 3 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን ገልጸው በ2016 በጀት ዓመት 11 ወራት 5 ቢሊዮን ብር ማጽደቁን ጠቁመዋል።

ባንኩ ለግብርና ኢንቨስትመንት ልዩ ትኩረት መስጠቱንና ይህንንም ለማሳካት ከክልሎች ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑን አመላክተዋል።

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ(ዶ/ር) በግብርና ኢንቨስትመንት የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት በቅርበት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያን የምግብ ሉዓላዊነት ማረጋገጥ ለጥያቄ የሚቀርብ አለመሆኑን ተናግረዋል።

ይህንንም ለማረጋገጥ ባለኃብቶች ያሉ አቅሞችን በሙሉ በመጠቀም ከተረጅነት የመውጣት ጉዞ አካል ሊሆኑ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

በሥራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት ሚኒስቴሩ ሁሌም ዝግጁ መሆኑንና አስፈላጊውን ድጋፍና እገዛ እንደሚያደርግም ጠቁመዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም