ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያው እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የተሻለ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማቅረብ  ያግዛል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ እያደገ የመጣውን የኃይል ፍላጎት ለማሟላትና የተሻለ ኃይል በማቅረብ ተደራሽነትን ለማስፋት የሚያስችል የኤሌክትሪክ ታሪፍ እየተዘጋጀ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ገለጸ።    

 በነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን አማካኝነት በተዘጋጀው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ ዙሪያ ከደንበኞች እና ከባለድርሻ አካላት ጋር ውይይትና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ ተካሂዷል።

 በዚሁ ወቅት በባለሥልጣኑ የክልል ኢነርጂና ብቃት ማረጋገጥ ድጋፍና ክትትል ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ግዛው በሥራ ላይ ያለው ታሪፍ ላለፉት ሁለት ዓመታት ለውጥ ያልተደረገበት በመሆኑ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱን ለኪሳራ መዳረጉን ገልጸዋል።

 በኃይል አቅራቢ ተቋማቶቹ ላይ የሚኖረውን አጠቃላይ ብክነት ለመቀነስ፤ የህብረተሰቡን የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል፤ የኢንዱስትሪዎችን የኃይል ፍላጎትን ለማሟላት ብሎም የኃይል መቆራረጥን ለመቀነስ የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል። 

 የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት እንዲሁም በሥርጭት ወቅት የሚባክነውን ኃይል ለመቀነስ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

 ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ሲተገበር የቆየው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ መጠናቀቁን ተከትሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለማሻሻያ መቆየቱ የኃይል አቅራቢ ድርጅቶችን ለኪሳራ እየዳረገ ይገኛል ብለዋል።

 ይህን ተከትሎ የኃይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋትና የኤሌክትሪክ ኤክስፖርትን ለመደገፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ጥናት አዘጋጅተው ለባለሥልጣኑ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።

 በመድረኩ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል እና አገልግሎት በቀጣይ የሚጠበቀውን ከፍተኛ የኃይል አቅርቦት ፍላጎት ለማሟላት ተጨማሪ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ቀርፀው እየሰሩ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

 ነገር ግን የተቋማቱ የፋይናንስ አቅም ውስን በመሆኑ ፍላጎቱን ለማሟላት የባለድርሻ አካላቱ የጋራ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ ተነስቷል።

 ማሻሻያው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትንና የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልን የፋይናንስ አቅም የሚያጠናክር እና ያለባቸውን የብድር ጫና ለመቀነስ የሚያግዝ መሆኑን ተናግረዋል። 

 በአማካይ 55 በመቶ የሚጠጋውን የአገሪቱን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሽፋን ወደ 74 በመቶ ለማሳደግ የህብረተሰቡና የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

 በውይይቱ የተሳተፉ አስተያየት ሰጪዎች አሁን ካለው ፍላጎትና የዋጋ ንረት አንፃር የታሪፍ ጭማሪው አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

 ነገር ግን ጭማሪው ተመጣጣኝ ሆኖ በሂደት እየጨመረ ቢሄድ የተሻለ እንደሚሆን ሃሳብ አቅርበዋል።

 አስተያየት ሰጪዎቹ የሚደረገው የታሪፍ ማሻሻያ ከዚህ በፊት የነበሩትን ችግሮች ለመቅረፍ የሚያስችል መሆን አለበት ሲሉ ተናግረዋል።

 ከጭማሪው ባሻገር በድርጅቶች ላይ የሚታየውን የኤሌክትሪክ መዋዠቅና የሚደርሰውን ጉዳት ማካካስን ታሳቢ ማድረግ አለበት የሚል ሀሳብ ሰጥተዋል።


 

 ከስድስት ዓመት በፊት የተሻሻለው የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ታሪፍ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማስፋት ማስቻሉን በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንሻል ማኔጅመንት ዳይሬክተር እና የታሪፍ ማሻሻያ ጥናት ቡድን አባል አቶ አለማየሁ መንግስቱ ተናግረዋል።

 የታሪፍ ማሻሻያው ለደንበኞች የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል፣ የኃይል ማመንጫ እና ማሰራጫ መስመር ግንባታዎችን ለማፋጠን የሚረዳ መሆኑን ገልጸዋል። 


 

 የአትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ስራ አስፈጻሚ ሽፍራው ተሊላ በበኩላቸው እየተዘጋጀ ያለው ታሪፍ በአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ ያሉትን ተግዳሮቶች እንደሚፈታ ተናግረዋል።

 ማሻሻያው የአገልግሎቱ ደንበኛ የሆኑ ተቋማትና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚያገኙትን የኃይል አቅርቦት በመጨመር አቅማቸውን እንደሚያሳድግላቸው ገልጸዋል።

 በኢነርጂ ዘርፉ የሚስተዋሉ ማነቆዎችን ለመፍታት የህብረተሰቡ ተሳትፎ አስፈላጊ መሆኑ በዚሁ ወቅት ተገልጿል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም