የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በልዩ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን የኢንቨስትመንት አማራጮች በልዩ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ ነው - የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያን በኢንቨስትመንት ተመራጭ ሀገር እንድትሆን የኢንቨስትመንት አማራጮችን በልዩ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ እየተሰራ መሆኑን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደገለጹት፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ይበልጥ ለመሳብ አማራጮችን በልዩ ሁኔታ የማስተዋወቅ ስራ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው ብለዋል።
በተለይ በግብርና፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪ፣ በአይሲቲ፣ በማዕድንና ቱሪዝም ላይ ያተኮረ ውጤታማ ስራዎች እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የኢንቨስትመንት መዳረሻዎችን የማስተዋወቅ ስራ በጥቅሉ ይደረግ የነበረ ሲሆን ከ2017 በጀት አመት ጀምሮ ግን ልዩ የኢንቨስትመንት መዳራሻዎች የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ ነው ያነሱት።
በመሆኑም የኢንቨስትመንት ማስተዋወቅ ስትራቴጂን በመከተል ኢትዮጵያን በዓለም ካሉ የኢንቨስትመንት መዳረሻዎች አንዱ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
ይህም የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በማሳለጥ የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ሁነኛ መፍትሄ መሆኑን ጠቁመዋል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ ወደ 29 ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የተለዩ ሲሆን ባለሀብቶች በተመቻቸላቸው ማበረታቻ ተጠቃሚ በመሆን በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ እንዲያለሙ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ከዚህም ባሻገር ለሀገር ውስጥ አልሚ ባለሀብቶችም ጭምር ትኩረት በመስጠት ኢትዮጵያውያን ኢንቨስተሮች በልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ እንዲያለሙ ማበረታቻ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
በበጀት አመቱ ባለፉት 10 ወራት 3 ቢሊዮን ዶላር ከውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት መሳብ መቻሉን ኮሚሽኑ መግለጹ ይታወሳል።