ቀጥታ፡

በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት ለንግድ ስርዓቱ መሳለጥ ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል 

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ በመዲናዋ በመከናወን ላይ ያለው የኮሪደር ልማት ለንግድ ስርዓቱ መሳለጥ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ነው ሲሉ የንግድ ማህበረሰብ አባላት ተናገሩ፡፡

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የአለም የዲፕሎማቲክ ማዕከል እና የኢትዮጵያ ርዕሰ  ከተማ ስትሆን በርካታ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ይከናወኑባታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከተማዋን በስሟ ልክ ለማድረግ፣ አለማቀፋዊነቷን የሚመጥን ቁመና ለማላበስና ለነዋሪቿ ምቹ ለማድረግ ሌት ተቀን ርብርብ እያደረገ ይገኛል፡፡

በዚህም "አዲስ አበባን እንደስሟ አዲስ እናደርጋለን" በሚል መሪ ሃሳብ በርካታ የልማትና የገጽታ ማሳመር ስራዎችን ሰርቷል፤ በመስራት ላይም ይገኛል።

ከነዚህ ስራዎች መካከል የኮሪደር ልማት አንዱ ሲሆን ዓላማው በከተማዋ የተገነቡ ትልልቅ መሰረተ ልማቶችን በማስተሳሰር የተሽከርካሪና የእግረኞች እንቅስቃሴ የተሳለጠ እንዲሆኑ ማድረግ ነው፡፡

የከተማዋን ገጽታ መቀየርና  የሰዎችን ኑሮ ማሻሻል ሌላኛው የልማቱ የትኩረት ማዕከል ነው፡፡

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ  የንግዱ ማህበረሰብ አባላት፤ የኮሪደር ልማቱ አስፈላጊ፣ ወቅቱን የዋጀ እና ለሌሎች ከተሞች በምሳሌነት የሚወሰድ ነው ብለዋል፡፡

የኢታአኮን ኮንስትራክሽን የግል ድርጅት ማኔጂንግ ዳይሬከተር ኢንጂነር አለማየሁ ንጋቱ እንደገለጹት፤  የትራፊክ መጨናነቅና የተበላሹ መንገዶች በንግድ እንቅስቃሴያቸው ላይ ከፍተኛ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።


 

ሸቀጦችን ከቦታ ቦታ በሚያዘዋውሩበት ወቅት በተበላሹ መንገዶች ምክንያት ላላስፈላጊ የገንዘብና የጊዜ ብክነት ይዳረጉ እንደነበር ተናግረዋል።

የኮሪደር ልማቱ ይህን ችግር በመፍታት ምቹ የሆነ የመንቀሳቀሻ ስፍራ በመፍጠር ሸቀጦችን እንደልብ ከቦታ ቦታ ለማዘዋወር የሚረዳ  እንደሆነ እምነታቸውን ገልጸዋል።

በመዲናዋ የተከናወኑና በመከናወን ላይ ያሉ የኮሪደር ልማት ለንግድ ስርዓቱ መሳለጥ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠሩ ታሳቢ ተደርገው እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት እያከናወነ ላለው ትውልድ ተሻጋሪ የልማት ስራ እኛ የንግዱ ማህበረሰብ አባላት የበኩላችን አስተዋጽኦ ለማበርከት ዝግጁ ነን ነው ያሉት፡፡

ከይሮ ኬብል ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የፋይናንስ ስራ አስኪጅ አቶ ግዛቸው መኮንን በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ ለከተማዋ ማህበረሰብ መሰረታዊ ለውጥ ያመጣ ነው ብለዋል፡፡


 

ከዚህ በፊት የነበረው የተሽከርካሪዎች ባገኙት ስፍራ ፓርክ ማድረግ በንግድ እንቅስቃሴው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድር እንደነበር ገልጸዋል፡፡

በመንግስት እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ይህን ችግር በዘላቂነት በማስቀረት የነዋሪዎችንና የንግድ ተቋማትን መስተጋብር የሚያሳደግ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

የኮሪደር ልማቱ ህጋዊ ነጋዴዎችን የሚያቀጭጩ ህገወጥ ንግዶችን በመከላከል ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው የገለጹት ደግሞ የቢዝነስ እና ኢንቨስትመንት ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር አማካሪ አቶ ይርጉ ታምሬ ናቸው፡፡

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም