ቀጥታ፡

ወቅቱን የዋጀ የስታትስቲክስ መረጃዎችን ለማውጣት የዘርፉ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ወቅቱን የዋጀ የስታትስቲክስ መረጃዎችንና ጥናቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ተማራማሪዎች ለማድረስ  የዘርፉ ባለሙያዎች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ  የኢትዮጵያ ስታትስቲክ አገልግሎት  ጥሪ አቀረበ።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር 32ኛ አመታዊ ጉባኤውን በአዲስ አበባ እያካሄደ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ስታትስቲክ አገልግሎት ዋና ዳሬክተር በከር ሻሌ(ዶ/ር) በጉባኤው ላይ እንዳሉት የሙያ ማህበሩ በስልጠና፣ በቴክኒካል ድጋፍና በሌሎች ዘርፎች ከአገልግሎቱ ጋር በቅርበት እየሰራ ነው።

አገልግሎቱ በስነ-ህዝብና ጤና፣ ግብርና እና የቤተሰብ ፍጆታ ወጪ ጥናት ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ዝግጅት እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው ፤ ለዚህም የሙያ ማህበሩ ትብብሩን የበለጠ እንዲያጠናክር ጠይቀዋል።

ወቅቱን የዋጀ የስታትስቲክስ መረጃዎችንና ጥናቶችን ለፖሊሲ አውጪዎችና ተመራማሪዎች ለማድረስ  የዘርፉ ባለሙያዎች የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

እንደ ዋና ዳሬክተሩ ገለጻ የኢትዮጵያ ስነ-ህዝብና ጤና ጥናት በዚህ ዓመት ለማጠናቀቅ ለመረጃ ሰብሳቢዎች ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

በቀጣይ ዓመት አጠቃላይ የግብርና ጥናት ለማድረግ ዝግጅት እየተደረገ ሲሆን በተመሳሳይ የቤተሰብ ፍጆታ ወጪ ጥናት ጎን ለጎን ለማካሄድ መታቀዱን ጠቁመዋል።

የጥናት ውጤቶች የፖሊሲ ውሳኔ ሰጪዎችና ተመራማሪዎች እንዲሁም በመረጃ ላይ ተመስርቶ በሚሰጥ ውሳኔ ፍትሃዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን ለማምጣት ያግዛሉ ብለዋል።

በመሆኑም የዘርፉ ሙያተኞች እንዲሁም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ለፕሮግራሞቹ መሳካት ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።


 

የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር ፕሬዝዳንት ዘይቱ ጋሻው(ዶ/ር) የስታትስቲክስ አገልግሎት ጥናት ለማድረግ እያከናወነ ላለው ተግባር አዳዲስ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴዎች ላይ ስልጠናዎችን በመስጠት በቅርበት እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

በቀጣይም በመረጃ ትንተና እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ዘርፎች በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

አለም እየተጠቀመበት ያለውን ዘመናዊ የመረጃ መሰብሰቢያ ዘዴ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ ማህበሩ የበኩሉን አስተዋጽኦ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።


 

በጉባኤው ላይ የተገኙት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ስታትስቲክ ማዕከል ዳሬክተር ተወካይ አንድሪ ኖንጉኢርማ( Andre Nonguierma) በበኩላቸው የተደራጀ የስታትስቲክስ መረጃ በአህጉሪቱ የተያዙ የልማት እቅዶችን ለማሳካት ፋይዳው የጎላ እንደሆነ አንስተዋል።

የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የአፍሪካ ስታትስቲክ አሰራር በቴክኖሎጂ ታግዞ እንዲደራጅና አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በአሰራር እየደገፈ መሆኑን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ ባለሙያዎች ማህበር እያካሄደ ያለው 32ኛ ዓመታዊ ጉባኤው ነገም የሚቀጥል ሲሆን በዘመናዊ የመረጃ አሰባሰብ ዘዴዎች ትግበራና ሌሎች ጉዳዮች ላይ ይመክራል ተብሏል።  

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም