17ተኛውን የአውሮፓ ዋንጫ የሚያስተናግዱትን 10 ስታዲየሞች እንተዋወቃቸው

የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ የሚታወቀው የአውሮፓ ዋንጫ ውድድር እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ1960 በፈረንሳይ አስተናጋጅነት መጀመሩ ይታወቃል፡፡

በመጀመሪያው የአውሮፓ ዋንጫ ሶቪየት ዩኒየን ዩጎዝላቪያን 2 ለ 1 በመርታት አሸናፊ የሆነችበት ውድድር ዘንድሮ ለ17ተኛ ጊዜ በጀርመን አስተናጋጅነት ከሰኔ 7 እስከ ሐምሌ 7 ቀን 2016 ዓ.ም ይከናወናል።

በውድድሩ 24 አገራት በስድስት ምድብ ተከፍለው ጨዋታቸውን የሚያከናውኑ ሲሆን እነዚህ ውድድሮች በጀርመን 10 ከተሞች በሚገኙ አሥር ስታዲየሞች ይከናወናሉ።

17 ተኛውን የአውሮፓ ዋንጫ የሚያስተናግዱትን 10 ስታዲየሞችን እንተዋወቃቸው፡-

የበርሊን ኦሊምፒክ ስታዲየም

በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን የሚገኝ ሲሆን 71ሺህ ተመልካች ይይዛል። የጀርመኑ ሀርታበርሊን ክለብ የሚጫወትበት ይኼ ስታዲየም 6 ጨዋታዎች የሚደረጉበት ሲሆን ስፔን ከክሮሽያ፣ ፖላንድ ከኦስትሪያ እና ኔዘርላንድ ከኦስትርያ የሚያደርጉትን የምድብ ጨዋታ፤ እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። በተጨማሪም የሩብ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ይደረጉበታል።

ሬንኢነርጂ ስታዲየም

ይህ ስታዲየም በጀርመኗ ኮሎኝ ከተማ ይገኛል። 43 ሺህ ተመልካች የሚይዝ ሲሆን የጀርመኑ ክለብ ኮሎኝ የሚጠቀምበት ስታዲየም ነው። በአውሮፓ ዋንጫው 5 ጨዋታዎቸን ያስተናግዳል። ሀንጋሪ ከሲውዘርላንድ፤ ስኮትላንድ ከሲውዘርላንድ፤ ቤልጂየም ከሮማንያ፤ ኢንግላንድ ከስሎቬኒያ እና እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። 

አሊያንዝ አሬና

ይህ ስታዲየም የጀርመኑ ክለብ ባየርሙኒክ የሚጫወትበት ስታዲየም ሲሆን፤ከ75 ሺህ ተመልካች በላይ ይይዛል። 6 ጨዋታዎች የሚደረጉበት ሲሆን ጀርመን ከስኮትላንድ፤ ሮማንያ ከዩክሬን፣ ስሎቬኒያ ከሰርቢያ፤ ዴንማርክ ከሰርቢያ፤ እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። በተጨማሪም አንድ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ያስተናግዳል።

ፍራንክፈርት አሬና

በጀርመኗ ከተማ ፍራንክፈርት የሚገኝ ሲሆን፤47 ሺህ ተመልካቾችን ይይዛል። የጀርመኑ ክለብ ኢንትራ ፍራንክፈርት የሚጠቀምበት ስታዲየም ሲሆን 5 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ቤልጂየም ከስሎቬክያ፤ዴንማርክ ከኢንግላንድ፣ ስዊዘርላንድ ከጀርመን፤ስሎቫኪያ ከሮማንያ የሚያደርጉትን የምድብ ጨዋታና እና እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል።

ቮልክ ስፓርክ

ይህ ስታዲየም በጀርመኗ ሀምቡሩግ ከተማ የሚገኝ ሲሆን 49 ሺህ ተመልካቾችን ይይዛል። የጀርመኑ ክለብ ሀምቡርግ የሚገለገልበት ሲሆን በአውሮፓ ዋንጫ 5 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል።ፖላንድ ከኔዘርላንድ ፤ክሮሽያ ከአልቤኒያ ፤ ጆርጂያ ከቼክሪፐብሊክ ፤ቼክ ሪፐብሊክ ከተርኪዬ የሚያደርጉትን የምድብ ጨዋታና ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል።

ሲግናል አዱና ፓርክ

ይህ ስታዲየም በጀርመኗ ዶርትሙንድ ከተማ የሚገኝ ሲሆን ከ81ሺህ በላይ ተመልካች ይይዛል። በቦሪሲያ ዶርትሙነድ ክለብ ባለቤትነት የተያዘው ስታዲየሙ 6 ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ጣሊያን ከአልቤኒያ፤ ተርኪዬ ከጆርጂያ፤ተርኪዬ ከፖርቹጋል ፣ ፈረንሳይ ከፖላንድ ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። በተጨማሪም አንድ የግማሽ ፍፃሜም ጨዋታም ያስተናግዳል።

ላይፕዚግ ስታዲየም

ይኼ ስታዲየም የጀርመኑ ክለብ አርቢ ላይፕዚግ የሚጫወትበት ሲሆን 40ሺህ ተመልካች ይይዛል ።በአውሮፓ ዋንጫው 4 ጨማታዎችን ያስተናግዳል። ፖርቹጋል ከቼክ ሪፐብሊክ ፤ ኔዘርላንድ ከፈረንሳይ ፤ክሮሽያ ከጣሊያን የሚያደርጉትን ምድብ ጨዋታ ጨምሮ ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። 

አሬና አፍሻልክ ስታዲየም

ይህ ስታዲም በጀርመኗ ከተማ ግላሰንከርከን ከተማ ይገኛል። የጀርመኑ ክለብ ሻልክ 04 የሚጠቀምበት ይህ ስታዲየም 50 ሺህ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን በውድድሩ 4 ጨዋታዎችን ያስተናግዳል። ሰርቢያ ከእንግሊዝ፤ ስፔን ከጣሊያን፤ጆርጂያ ከፖርቹጋልና እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል። 

ስቱትጋርት አሬና

ይህ ስታዲም በጀርመኗ ከተማ ስቱትጋርት የሚገኝና የጀርመኑ ክለብ ስቱትጋርት የሚጠቀምበት ስታዲየም ነው። ስሎቬኒያ ከዴንማርክ፤ጀርመን ከሀንጋሬ፤ስኮትላንድ ከሀንጋሬ፤ዩክሬን ከቤልጂየም የሚያደርጉትን የምድበ ጨዋታዎች ፣በተጨማሪም አንድ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታን ያስተናግዳል።

ዱሴልዶርፍ አሬና

በጀርመኗ ከተማ ዱሴልዶርፍ የሚገኝ ሲሆን 47 ሺህ ተመልካች የመያዝ አቅም አለው።ስታዲየሙ 5 ጨዋታዎችን የሚያስተናግድ ሲሆን ኦስትርያ ከፈረንሳይ፤ስሎቬኪያ ከዩክሬን፤አልቤኒያ ከስፔን የሚያደርጉትን የምድብ ጨዋታና እንዲሁም ከ16 ቱ የጥሎ ማለፍ ጨዋታዎች አንዱን ያስተናግዳል።። በተጨማሪም አንድ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ይደረግበታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም