በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 220 ወረዳዎች ላይ በንቅናቄ የታገዘ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ ይከናወናል - ጤና ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
በሀገር ዓቀፍ ደረጃ 220 ወረዳዎች ላይ በንቅናቄ የታገዘ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ ይከናወናል - ጤና ሚኒስቴር
ሚዛን አማን፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ በቀጣይ ስድስት ወራት በሀገር ዓቀፍ ደረጃ በ220 ወረዳዎች ላይ በንቅናቄ የታገዘ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እንደሚከናወን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ወቅታዊ የወባ ስርጭትን በዘላቂነት ለመግታት ያለመ ሀገር አቀፍ የምክክር መድረክ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ሚዛን አማን ከተማ እየተካሄደ ነው።
የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፣ እየጨመረ ያለውን የወባ በሽታ ስርጭት ለመቀነስ በቀጣይ ስድስት ወራት ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል።
የመከላከሉን ሥራ ባለድርሻ አካላትና በየደረጃው ያለው አመራር ቀዳሚ አጀንዳው አድርጎ እንዲመራ ዛሬ የንቅናቄ መድረክ መጀመሩን ገልጸዋል።
ለቀጣይ ስድስት ወራትም እንደሀገር በ220 ወረዳዎች ላይ በንቅናቄ የታገዘ የወባ በሽታ መከላከል ሥራ እንደሚከናወን አስታውቀዋል።
በአሁኑ ወቅት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ፣ በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች ላይ የበሽታው ስርጭት ጎልቶ እንደሚታይም ጠቅሰዋል።
የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው የወባ በሽታ የሚያስከትለውን ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጫና ለመቀነስ በቅንጅት መሥራት ይገባል ብለዋል።
በክልሉ የሚስተዋለው ከፍተኛ የወባ ስርጭትን ቀድሞ መከላከል ላይ እያጋጠሙ ያሉ ተግዳሮቶች ለይቶ ማረም እንደሚገባ ገልጸዋል።
እንደ ክልል ምርታማ እና አምራች የሰው ኃይል ለማፍራት ጤና መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ የወባ በሽታ እያስከተለ ያለውን ጫና ለመቀነስ በትኩረት ይሰራል ብለዋል።
ክልላዊ የወባ በሽታ ስርጭት እየጨመረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኢብራሂም ተማም ናቸው።
በክልሉ ወባን ለመከላከል ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ የአልጋ አጎበር መሰራጨቱን አስታውሰው፣ ከ117 ሺህ በሚበልጡ ቤቶች ላይ የጸረ ወባ ትንኝ ኬሚካል ርጭት ተከናውኗል ብለዋል።
በሚዛን አማን ከተማ ለሁለት ቀናት እየተካሄደ ባለው የምክክር መድረክ ላይ ከፌዴራልና ከክልሎች የመጡ ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።