ቀጥታ፡

በተመዘገቡ ስኬቶች ሳንኩራራ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነትና በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት አለብን -ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፦ በተመዘገቡ ስኬቶች ሳንኩራራ የኢትዮጵያን የብልፅግና ጉዞ ለማሳካት በቁርጠኝነትና በጊዜ የለንም መንፈስ መስራት አለብን ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የ2016 በጀት ዓመት ያለፉት 10 ወራት የማክሮ ኢኮኖሚና የዘርፎች ዋና ዋና አፈጻጸም እና የ2017 የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት እየተደረገ ነው።

በመድረኩ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ማስተባበሪያ ማዕከል ሃላፊ አደም ፋራህ፣ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) ሌሎች ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የተቋማት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፣ ባለፉት 10 ወራት የተመዘገቡ ውጤቶች በዓመቱ የተተነበየውን የ7 ነጥብ 9 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ማሳካት እንደሚቻል የሚያሳዩ ናቸው።

መንግስት ኢትዮጵያ መበልፀግ አለባት የሚል ትልቅ ራዕይ ይዞ እየሰራ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህንንም ማሳካት የሚያስችሉ በርካታ ምቹ ሁኔታዎች አሉ ብለዋል።

የማድረግ አቅምን በመጠቀም ባለፉት ዓመታት በበጋ ስንዴ፣ በሩዝ ልማት፣ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋት፣ በኢትዮጵያ ታምርትና ሌሎችም የተገኙ ውጤቶችን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት ተርታ መሰለፍ የሚያስችላትን ጉዞ በአግባቡ እየከወነች መሆኗንም እንዲሁ።

በዚህ ዓመት ኢትዮጵያ ከዓለም 57ኛ፣ ከአፍሪካ አምስተኛ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚ ባለቤት መሆኗን የዓለም አቀፍ ተቋማት ማረጋገጣቸውን አንስተዋል።


 

ኢትዮጵያን ወደ ብልጽግና ማማ ማሻገር የሚያስችሉ እምቅ የተፈጥሮ ሃብቶችና አምራች ኃይል መኖሩን ጠቅሰው አመራሩም የዕይታና የስራ ባህል ለውጥ በማድረግ በትጋት መስራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በድል የመርካትና የመጠበቅ ችግርን በመቅረፍ በሁሉም መስክ ቀጣይነት ያለው ድል ለማስቀጠል መትጋት ይገባል ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሀገር ጉዳይ በባለቤትነት መንፈስ በትብብር በመስራት ችግሮችን በጋራ መሻገር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሀገርን ትልም ለማሳካት ምርታማነትን ማሳደግ፣ የለውጥ ስራዎችን ማስቀጠል፣ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርምን በሁሉም ተቋማት መተግበር እና ሰላምን ማጽናት ቀጣይ ትኩረቶች እንደሆኑም ገልጸዋል።

የ2016 በጀት ዓመት የ10 ወራት ዋና ዋና የኢኮኖሚ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀረቡት የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በበጀት ዓመቱ የታቀደውን አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት ማስመዝገብ እንደሚቻል አመላካች ውጤቶች መኖራቸውን ገልጸዋል።

ለዚህም በግብርና፣ በኢንዱስትሪና በአገልግሎት ዘርፍ የተሻለ ውጤት መመዝገቡን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

 

 

 

 

 

 

 


 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም