ቀጥታ፡

 ለወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥ የሎጂስቲክስ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተገለጸ

ድሬዳዋ ፤ ሰኔ 7/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ለወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥና ተደራሽነት የሎጂስቲክስ ሥራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገለጸ።

በስምንት ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር የተገነባውና የድሬዳዋ ደረቅ ወደብ እና ተርሚናልን ከከተማው ዋና መንገድ ጋር የሚያገናኘው መንገድ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።

በኢትዮጵያ የባህርና ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረትአብ ተክሉ እና የጭነት አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲራጅ አብዱላሂን ጨምሮ የሎጀስቲክሱና የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ የአመራር አባላት መንገዱን ሥራ አስጀምረዋል።

የወደብና ተርሚናል ዘርፍ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረትአብ ተክሉ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ለወጪና ገቢ ንግድ መሳለጥ ጠቀሜታ ያላቸውን የሎጂስቲክስ ሥራዎችን አጠናክሮ ይቀጥላል። 


 

በተለይም የወጪና ገቢ ንግድ ለማሳለጥና ተደራሽ ለማድረግ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው የአገሪቷ ክፍሎች የደረቅ ወደብና ተርሚናል ግንባታዎችን ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል።

አንድ ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና ዛሬ የተመረቀው የኮንክሪት አስፋልቱ ከዋና መንገድ እና ከነፃ ንግድ ቀጣና ጋር የሚያገናኝና የደረቅ ወደብና ተርሚናሉን ሁለንተናዊ የአገልግሎት አሰጣጥና ጠቀሜታ የሚያሳደግ መሆኑን ገልፀዋል።

በምረቃው ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ተወካይና የአስተዳደሩ የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሙሉካ መሐመድ በበኩላቸው፤ በድሬዳዋ እየተገነቡ የሚገኙ ግዙፍ መሠረተ ልማቶች የአገራችንን የምስራቅ ቀጣና የንግድና የኢንዱስትሪ ማሳለጫ መሆኗን እያረጋገጡ ናቸው ብለዋል።


 

ዛሬ የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናልን ከከተማው ዋና መንገድ የሚያገናኘው መንገድ  ተገንብቶ አገልግሎት መጀመሩም የጉዞው ስኬታማነት ማሳያ መሆናቸውንም ገልጸዋል።

እነዚህ ግዙፍ ሃብቶች ኢኮኖሚውና ማህበራዊ ትስስሩን በሚፈለገው ደረጃ ከፍ እንዲያደርጉ አስተዳደሩ በአካባቢው የተለያዩ ዘመናዊ የአገልግሎት ማዕከላትን በመገንባት የህዝቡን ተጠቃሚነት ያሳድጋል ብለዋል።

ከደረቅ ወደቡ ተጠቃሚ ሾፌሮች መካከል የከባድ መኪና አሽከርካሪ አቶ ዘነበ ኃይለስላሴ እንዳሉት፤ መንገዱ ቀደም ሲል በተሽከርካሪዎች ላይ ይደርስ የነበረን ጉዳት የሚቀንስ በመሆኑ ዘላቂ ጥቅም እንዲሰጥ የድርሻቸውን ይወጣሉ።

በቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን ለተገነባው የኮንክሪት አስፋልት ስራ ላይ አስተዋፅኦ ለነበራቸው ተቋማት የዕውቅና የምስክርነት ወረቀት ተሰቷቸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም