ቀጥታ፡

ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ ጋር በአፈር ማዳበሪያ ዝውውር አፈጻጸም ዙሪያ ተወያየዩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 7/2016(ኢዜአ)፡- የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ ጋር በአፈር ማዳበሪያ ዝውውር አፈጻጸም ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

የማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴው ባቀረበው ሪፖርት እስከአሁን 27 የአፈር ማዳበሪያ የጫኑ መርከቦች ጅቡቲ መድረሳቸውንና የ24 መርከቦች የአፈር ማዳበሪያ ጭነት ከጅቡቲ ወደብ ወደ ኢትዮጵያ እየተጓጓዙ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀሪዎቹ 3 መርከቦች በኦፕሬሽን ላይ እንደሚገኙ ኮሚቴው አስታውቋል።


 

በዘህ መሰረት እስከአሁን 1 ሚሊየን 334 ሺህ 487 ነጥብ 1 ሜትሪክ ቶን የአፈር ማዳበሪያ ማጓጓዝ በመቻሉ ከዓመታዊ እቅድ 68 ነጥብ 78 በመቶ መሳካቱን ኮሚቴው ገልጿል።

የትርንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) እስከአሁን በተሰሩ የማጓጓዝ ስራዎች ኮሚቴውን አመስግነዋል።

አሁንም የአፈር ማዳበሪያ ጉዳይ የሞት የሽረት ጉዳይ መሆኑን በመረዳት ኮሚቴው በማጓጓዝ ሂደቱ ላይ ያጋጠሙ ችግሮች ተቀርፈው ቀሪ የማዳበሪያ ጭነቶች በተጠናከረ መልኩ ተቀናጅቶ በመስራት በወቅቱ ለአርሶ አደሮች ማድረስ እንዲቻል አቅጣጫ ሰጥተዋል።


 

በበጀት አመቱ የገቢ-ወጪ ምርትን ለማሳለጥ የተቋቋመው የአፈር ማዳበሪያ ኦፕሬሽን ኮሚቴ በኤምባሲው ሰብሳቢነት ከትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ባህርና ሎጂስቲክስ፣ ከኢትዮ-ጅቡቲ ምድር ባቡር፣ ከኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን፣ ከጉምሩክ ኮሚሽን እና ከኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት በመዋቀር በሳምንት ሁለት ጊዜ በኤምባሲው ተገኝቶ የአፈር ማዳበሪያ ዝውውሩን ሲገመግም መቆየቱን በጅቡቲ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም