የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑ ተገለጸ ።
የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያን በተመለከተ ከሚዲያና ኮሙኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት አካሂዷል።
በመድረኩ ላይ ንግግር ያደረጉት የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ፤ የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ አግባብ እንዲከናወን እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽነትን ለማስፋት የታሪፍ ማሻሻያ ማድረግ እንዲሁም በሥርጭት ወቅት የሚባክነውን ለመቀነስ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።
ከ2011 እስከ 2014 ዓ.ም ሲተገበር የቆየው የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያ መጠናቀቁን ተከትሎ ላለፉት ሁለት ዓመታት ያለማሻሻያ መቆየቱ የኃይል አቅራቢ ድርጅቶችን ለኪሳራ እየዳረገ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም ምክንያት ኃይል አቅራቢ ተቋማትን ለኪሳራ እየዳረገ መሆኑን አንስተው፤ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
በመሆኑም የኃይል አቅርቦት አማራጮችን ለማስፋትና የኤሌክትሪክ ኤክስፖርትን ለመደገፍ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የታሪፍ ጥናት አዘጋጅተው ለባለሥልጣኑ ማቅረባቸውን ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ቅድመ ግምገማ እያከናወነ መሆኑንና የሕዝብ አስተያየት የመቀበል ሂደት በተለያየ መንገድ እየተከናወነ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የፋይናንስ ማኔጅመትን ዳይሬክተር አለማየሁ መንግስቱ፤ የኃይል አቅራቢ ተቋማቱ የውስጥ አሠራርን ማሻሻል፣ በዝቅተኛ ወለድ ብድር ለማግኘትና የፋይናንስ ጤናማነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋትና አስተማማኝ ኤሌክትሪክ ለማቅረብ የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ ስለመሆኑ አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አሸብር ባልቻ፤ በዓለም ላይ ካለው ገበያ ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን የታሪፍ ማሻሻያው አስፈላጊ መሆኑን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽፈራው ተሊላ በበኩላቸው፤ የታሪፍ ማሻሻያው ተቋሙ የኃይል ተደራሽነትን ለማስፋት ለያዛቸው ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ ወሳኝ መሆኑን አንስተዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የታሪፍ ማሻሻያው የተቋማቱን ህልውና በማስጠበቅ ለተሻለ የኃይል ልማትና ተደራሽነት ወሳኝ መሆኑን ገልፀዋል።
የታሪፍ ማሻሻያውም በብዙ መልኩ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል::
የኃይል አቅራቢ ተቋማቱም የታሪፍ ማሻሻያው ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ያሉ ዜጎችን መደጎም በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን አረጋግጠዋል።