ቀጥታ፡

የፌዴራል ፖሊስ ከናይጄሪያ የጦር ኮሌጅ ጋር የልምድ ልውውጥ አደረገ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 06/2016(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ከናይጄሪያ ፌደራል ሪፐብሊክ የጦር ኮሌጅ ጋር “የማዕድን ዘርፍን መጠበቅ ለተጠናከረ ብሄራዊ ደህንነት” በሚል ርዕስ በዋና መሥሪያ ቤት የልምድ ልውውጥ አደረገ።

የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል በናይጄሪያ የፌደራል ሪፐብሊክ ጦር ኮሌጅ አዛዥ ሜጀር ጀነራል አይቢ ማይና ለሚመራው ልዑክ አቀባበል አድርገውላቸዋል።

በልምድ ልውውጡ ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል ጥንታዊት፣ የአፍሪካ የነጻነት ምልክት የሆነችው እና በሕዝብ ብዛት ከናይጄሪያ ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ በርካታ ማዕድናት ያሏት እና የመንግስት ፖሊሲና መመሪያ በመሻሻሉ ምክንያት ለልማት ከፍተኛ አቅም መፍጠሯን ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ በሀገርና በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማዕድን አምራች ባለሀብቶች ተመራጭ መዳረሻ መሆኗን የገለፁት ኮሚሽነር ጀነራል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በማዕድን ምርት ላይ ጉልህ ጭማሪ መታየቱንም ተናግረዋል፡፡

እነዚህን ሀብቶች ከሕገ-ወጥ ብዝበዛና ዝውውር መጠበቅ ለሀገር ደኅንነት ወሳኝ ሚና እንዳለውም አንስተዋል፡፡

ሕገ-ወጥ የማዕድን ሥራ ግጭትን እንዳያባብስ፣ የተደራጁ ወንጀሎችን ተጠናክረው በአካባቢው ማህበረሰብ ሕይወት ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድሩ የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለዘርፉ ትልቅ ትኩረት በመስጠት ኃላፊነት ያለው አስተዳደር ለማረጋገጥ ከባለድርሻ አካላት እና ከተለያዩ ሀገራት ጋር በቁርጠኝነት እየሠራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ፖሊስን ተቋማዊ አቅምን ለማጠናከር እያካሄደ ባለው የሪፎርም ሥራ የባለሙያን ቁጥር በመጨመር የቴክኖሎጂ አቅሙን በከፍተኛ ደረጃ ማሳደጉንም አስረድተዋል፡፡ 

በተቋማዊ ሪፎርም የፈጥኖ ደራሽ ፖሊስ ኃይል፣ የአድማ መከላከል ፖሊስ፣ የተቋማዊ ደህንነት ፖሊስ፣ የዩኒቨርሲቲ ፖሊስ፣ የማዕድን እና ቱሪዝም፣ የአቪዬሽን ደህንነት ፖሊስ፣ የምድር ባቡር ፖሊስ፣ የኢንዱስትሪ ፖሊስ እና ሌሎች የሥራ ክፍሎች እንደ አዲስ መደራጀታቸውን አብራርተዋል፡፡

በናይጄሪያ የፌደራል ሪፐብሊክ ጦር ኮሌጅ አዛዥ ሜጀር ጀነራል አይቢ ማይና የተመራው ልዑካን ቡድን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የቴክኖሎጂ አቅሞችን ተዘዋውረው መጎብኘታቸውን ከፌዴራል ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም