ቀጥታ፡

አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ጋር ተወያዩ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ፣ የእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና ቀይ ባህር ልዩ ልዑክ አሊሰን ብላክበርንን በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።

አምባሳደር ምስጋኑ በተመሳሳይ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕ ጋርም በኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።

ሚኒስትር ዴኤታው ከእንግሊዝ የአፍሪካ ቀንድ እና የቀይ ባህር ልዩ ልዑክ አሊሰን ብላክበርን ጋር ባደረጉት ውይይት ሁለቱ ሀገራት ባላቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ሁኔታ፣ በአፍሪካ ቀንድ ቀጣና ዙሪያ ባሉ የሰላምና ፀጥታ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ልማት ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል።


 

በተለይም የእንግሊዝ መንግስት በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን እንዲሁም ንግድና ኢንቨስትመንትን በማስፋፋት ረገድ ማገዝ በሚችልባቸው ሁኔታዎች ላይ የሀሳብ ልውውጥ ማድረጋቸው ተገልጿል።

በውይይቱ ልዩ ልዑኳ በኢትዮጵያ እየተከናወኑ ያሉ የሽግግር ፍትህ እና ሀገራዊ ምክክር ጥረቶችን የሀገራቸው መንግስት ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆኑን አስታውቀዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በኢትዮጵያ የኦስትሪያ አምባሳደር ሲሞን ክናፕ ጋር ባደረጉት ውይይትም በኢትዮጵያ እና ኦስትሪያ መካከል ያለውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ መክረዋል።

አምባሳደር ምስጋኑ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ታሪካዊ ግንኙነት በተለያዩ መስኮች በተለይም በኢኮኖሚው ዘርፍ የበለጠ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

አምባሳደር ክናፕ በበኩላቸው የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ እንዲሁም የኦስትሪያ የቢዝነስ ልዑካን ቡድን በመጭው ጥቅምት ወር በኢትዮጵያ ጉብኝት ለማድረግ ያለውን እቅድ አብራርተዋል።

ሁለቱ ወገኖች በኦስትሪያ የንግድ ተቋማት እና በኢትዮጵያውያን አቻዎቻቸው መካከል የልምድ ልውውጥ ማድረግ አስፈላጊ መሆኑን መግለጻቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

የኢትዮጵያ ማዕድን ሚኒስቴርንና ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን በኦስትሪያ ከሚገኙ የሚመለከታቸው አካላት ጋር በማስተሳሰር በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ኢትዮጵያውያንን አቅም ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይም መወያየታቸው ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም