ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፤ሰኔ 06/2016 (ኢዜአ)፦ ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠንና ኢንቨስትመንትን በመሳብ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግር የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዳማና ሞጆ ከተሞች መካከል በ24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ግንቦት 2/2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወቃል።
ይህንንም ተከትሎ ዛሬ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሺነር ዘለቀ ተመስገን እና የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚነት ስምምነት ተፈራርመዋል።
የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን በዚሁ ወቅት፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የተመሰረተበት ዋና አላማ ኢትዮጵያ የማይበገር ኢኮኖሚ እንድትገነባ ለማስቻል ነው ብለዋል።
በዚህም፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ የኢንዱስትሪ ሽግግርን በማፋጠን ኢትዮጵያ በዓለምአቀፍ ንግድ የተጠናከረ ትስስር እንዲኖራት የሚያደርግ መሆኑን ገልጸዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ ለወጣቶች የስራ እድልን በመፍጠር ረገድም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸዋል።
እንዲሁም ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ጭምር የተመሰረተ ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ሰፊ ስራ እየሰራ ነው።
በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ እያስገባ ነው ብለዋል።
ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች በልዩ ልዩ መስኮች ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።
ኮሚሽኑ በቅርቡ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ወጥቶ ወደ ስራ እንዲገባ ያደረገ ሲሆን ከገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ጋር የተደረሰው "የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚነት" ስምምነትም አዋጁን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል።
ልዩ የኢኮኖሚ ዞኑ በ120 ሚሊዮን ዶላር ግንባታው እየተከናወነ ሲሆን፥ የሎጅስቲክስ ፓርኮች፣ ነጻ የንግድ ቀጠና ማዕከሎች፣ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የወጪና ገቢ ንግድ ማዕከል፣ የመንገድ ግንባታ፣ የሪል ስቴት፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።