ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በአቪዬሽን ደህንነት ዘርፍ ምንም አይነት ስጋት እንደሌለባት ተረጋገጠ

አዲስ አበባ፤ሰኔ 06/2016 (ኢዜአ)፦ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አካል በሆነው የዓለም አቀፉ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኦዲት ባለሙያዎች የተደረገው የኢትዮጵያ አቪዬሽን ደህንነት ኦዲት ውጤት ይፋ ሆኗል። 

የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ደህንነት ዓለም አቀፍ ኦዲት በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት /አይሲኤኦ/ የኦዲት ባለሙያዎች አማካይነት ከግንቦት 26/ 2016 ዓም ጀምሮ በአዲስ አበባ ሲካሄድ ቆይቷል።

የኦዲት ስራው መጠናቀቁን ተከትሎ የኦዲት ስራውን ያስተባበረው የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሲቪል አቪዬሽን ደህንነት መምሪያ ዳይሬክተር አቶ አስራት ቀጀላ  ውጤቱን ዛሬ ይፋ አድርገዋል። 

የኢትዮጵያ አቪየሽን ደህንነት ኦዲት በተለያዩ ምክንያቶች ሳይደረግ ቢቆይም ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መካሄዱን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የአየር ትራንስፖርትን እ.አ.አ በ1946 ከአዲስ አበባ-ካይሮ በተደረገው ታሪካዊ በረራ የጀመረች ሲሆን፥ ለዓለም አቀፋ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅል አባል ከሆኑ እና በአቪዬሽን ዘርፍ ቀዳሚ ሀገራት አንዷ መሆኗን ገልፀዋል።

ባለፉት ዓመታት በአቪየሽን ኢንዱስትሪው ከፍተኛ የሪፎርም ስራዎች  መከናወናቸውን አብራርተዋል።

ከሰሞኑ በዘጠኝ ኦዲት ዘርፎች በከፍተኛ ባለሙያዎች ጥልቅ ዳሰሳዎች መደረጉን ገልፀው፣ የቦሌ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ በኤርፖርቶችና በህግ ማዕቀፍ ሁለንተናዊ ቅኝቶች መደረጋቸውን አስረድተዋል።

የባለሙያዎች ኦዲት ውጤቱም ኢትዮጵያ ምንም አይነት የአቪዬሽን ደህንነት ስጋት እንደሌለባት ያረጋገጠ መሆኑን ይፋ አድርገዋል።

ምንም አይነት የአቪዬሽን ዘርፍ ደህንነት ስጋት እንደሌለ መረጋገጡ ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ተደራሽነቱን ለማስፋፋት እና ለኢትዮጵያ ትልቅ ድልና ዕድል መሆኑንም ተናግረዋል።

ግኝቱ የኢትዮጵያን ቀደምት ስምና ታሪኳን የሚመጥን መሆኑን ገልፀው፣ ይህም በአቪዬሽን ዘርፉ ለሚሰማሩ ኩባንያዎች ትልቅ ዋስትና እንደሆነም ነው ያነሱት። 

ለዚህ ስኬት ዕውን መሆን ጉልህ ሚና ያበረከቱ ተቋማት እና አመራሮችንም አመስግነዋል። 

በቀጣይም ደህንነቱ የተጠበቀ የአቪየሽን ደህንነት የመገንባት ጥረቱ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተናገሩት።

ዝርዝር የኦዲት ውጤቱን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ በዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት በኩል ይፋ እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም