ቀጥታ፡

26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን አብሮነትና አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ይከበራል- አቶ ኦርዲን በድሪ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ) :- 26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ቀን አብሮነትና አንድነትን በሚያጎለብት መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የሀረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለፁ።

26ኛው አለም አቀፍ የሀረር ስፖርትና ፌስቲቫል ለማክበር የተቋቋመው ኮሚቴ ለበዓሉ እየተደረጉ የሚገኙ ዝግጅቶችን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር በተገኙበት ገምግሟል።

በዓሉ የተሳካ እንዲሆን የተለያዩ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ወደ ስራ የገቡ ሲሆን ከቦታ ልየታ ጀምሮ ለበአሉ አስፈላጊው ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝም ተመላክቷል።


 

በዓሉ በሲምፖዚየም፣ የንግድ ትርዒት እና ባዛር፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ ስፍራዎች ጉብኝት፣ በአረንጓዴ አሻራ መርሃግብር፣ የልማት ፕሮጀክቶች ምረቃ እና ሌሎች መርሀ ግብሮች እንደሚከበርም ተገልጿል።

በዓሉ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበር ለማስቻልም ከፌዴራል እና አጎራባች ክልል የፀጥታ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑን ኮሚቴው አስታውቋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ እንዳሉት በዓሉ አንድነት እና አብሮነትን በሚያጠናከር ብሎም ዘላቂ ሰላም እና ልማትን በሚያረጋግጥ መልኩ ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል።

በተለይ በዓሉ በክልሉ መከበሩ ዲያስፖራው ማህበረሰብ በአገሩ ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በተግባር እንዲገነዘብ ከማድረግ አንፃር ትልቅ አበርክቶ እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በበዓሉ ወቅት የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስመረቅ እየተሰራ እንደሚገኝ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ በሂደት ላይ የሚገኙ የልማት ስራዎችን በተያዘላቸው ግዜ ለማጠናቀቅ ርብርብ ሊደረግ ይገባል ብለዋል።

አሁን ላይ ተግባራዊ እየተደረጉ የሚገኙ የከተማ ፅዳት ውበት እና አረንጓዴ ልማት ስራዎች ግለታቸውን ጠብቀው እንዲቀጥሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አቅጣጫ ማስቀመጣቸውን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም