በኢትዮጵያ እስካሁን 620 የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ስርዓት ገብተዋል - ዶክተር በለጠ ሞላ - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ እስካሁን 620 የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ስርዓት ገብተዋል - ዶክተር በለጠ ሞላ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ለማፋጠን በተሰሩ ስራዎች እስካሁን 620 ሀገራዊ የመንግስት አገልግሎቶች ወደ ዲጂታል ስርዓት ማስገባት መቻሉን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ተካሂዷል።
በመድረኩ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ዲጂታል ትራንስፎርሜሽን መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ በለጠ ሞላ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ከሚኒስቴሩ ቁልፍ ተልዕኮዎች አንዱ የዲጂታላይዜሽን ትግበራውን ማፋጠንና ማስፋፋት መሆኑን አንስተዋል።
የዲጂታል ስትራቴጂና ፖሊሲ ተቀርጾ የመንግስትን ተቋማት አገልግሎት ወደ ኤሌክትሮኒክ ወይም ዲጀታል ስርዓት ለማስገባት ትኩረት ተደርጎ መሰራቱን ገልጸዋል።
እስካሁን 620 ሀገራዊ የመንግስት አገልግሎቶች በዲጂታል ስርዓት እንዲገቡ መደረጉን አስረድተዋል።
በቀጣይም የመንግስት አገልግሎቶችን ወደ ዲጂታል ስርአት የማስገባት ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
ቴሌኮምን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የሀገራዊ የዲጂታል እንቅሰቃሴ ከፍተኛ እምርታ የመጣበት መሆኑን ጠቅሰው፤ እስካሁንም ከስድስት ትርሊዮን ብር በላይ የዲጂታል ፋይናንስ እንቅስቃሴ መደረጉን ተናግረዋል።
የዲጀታል ኢኮኖሚ ግንባታን ዕውን ለማድረግም በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ሚኒስቴሩ በኢኖቬሸንና ምርምር ዘርፍ ረገድ በጤና፣ በማምረቻ፣ በግብርናና በሌሎችም ዘርፎች ችግር ፈች የሆኑ የምርምር ውጤቶች ተደራሽ የማድረግ እና ቴክኖሎጂ የማላመድ ስራዎችን ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት ማከናወኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም በስታርአፕ ምሕዳሩን ለማስፋት በተሰሩ ሰፋፊ የድጋፍ ስራዎች ተሰፋ ሰጭ ውጤቶች ስለመገኘታቸው ጠቅሰዋል።
በተጠሪ ተቋማት በኩል በሚሰሩ የምርምር ስራዎች ረገድም መልካም ውጤቶች እንደተገኙ በግምገማ እንደተረጋገጠ አንስተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ዕውን ለማድረግ የሚያስችሉ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ስራዎች እና በክህሎት ተኮር የዲጂታል ልማት ላይ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ሚኒስቴሩ በቅርቡ ከአጋር አካላት ጋር በመተባበር የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን የዲጂታል ክህሎት አቅም ለመገንባት በመጀመሪያ ዙር 10 ሺህ ወጣቶች ተጠቃሚ የሚያደርግ ኤኒሸቲቭ መጀመሩን ገልጸዋል።
ዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ዕውን ለማድረግ ወጣቶች ላይ መስራት ወሳኝ ጉዳይ በመሆኑ እስከ አንድ ሚሊዮን ወጣቶችን በዚህ ኢኒሸቲቭ ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት እንደሚቀጠል አረጋግጠዋል።