ቀጥታ፡

ባለፉት አስር ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል - ሙፈሪያት ካሚል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦ በ2016 በጀት ዓመት ያለፉት አስር ወራት ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በሀገር ውስጥና በውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል ተናገሩ።

ሚኒስትሯ እንደተናገሩት፤ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር ለሥራ የሚሰማሩ ዜጎች ተፈላጊውን ክህሎት እንዲጨብጡ የማብቃት ተግባር ትኩረት ተሰጥቶታል።

በተለይም የሰለጠነ የሰው ኃይል ወደ ውጭ ለማሰማራት አስፈላጊው ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አስታውሰው፥ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ ብቁ ስለመሆናቸው የምስክር ወረቀት እንዲያገኙ እየተደረገ ነው ብለዋል።

እንደ ሚኒስትሯ ገለጻ በበጀት ዓመቱ አስር ወራት 314 ሺህ ዜጎች የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ተጠቃሚ ሆነዋል።

የሥራ ስምሪቱ ዜጎች ደህንነታቸው፣ የሚያገኙት ጥቅምና መብታቸው ተጠብቆ እንዲሰሩ በሚያስችል መልኩ መከናወኑንም አብራርተዋል።

በሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል ፈጠራ ከ2 ነጥብ 7 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰው በጥቅሉ ለ3 ሚሊዮን 77 ሺህ ዜጎች የሀገር ውስጥና የውጭ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል።

ሚኒስትሯ እንዳሉት የዲጂታል ሥርዓት በመዘርጋት ዜጎች ተመዝግበው ወደ ሥራ ገበያው እንዲገቡ ለማድረግ ምቹ ሁኔታዎችን መፍጠር ላይም በትኩረት እየተሰራ ነው።

በቴክኒክና ሙያ ዘርፍም ወጣቶች ያላቸውን የፈጠራ ሀሳብ ወደ ቴክኖሎጂ ምርት መቀየር የሚችሉበት ስልጠና እና ምቹ ምህዳር መፈጠሩንም አክለዋል።

በዚህም የስራ ሀሳብ ያላቸው ወጣቶችን በማወዳደር ምርቶቻቸውን ለሀገር ኢኮኖሚ ዕድገት እንዲጠቀሙ በተጀመረው ሂደት 76 ቴክኖሎጂዎች ወደ ምርት መሸጋገራቸውን አብራርተዋል።

ስታርትአፖችና ኢንተርፕራይዞችን በማጎልበት ተጨማሪ የስራ ዕድል እንዲፈጥሩ በመንግስት ትኩረት መደረጉን አስረድተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም