ቀጥታ፡

ባለፉት አስር ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት ተችሏል- አቶ መላኩ አለበል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦ በበጀት ዓመቱ ባለፉት አስር ወራት 2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በአገር ውስጥ መተካት መቻሉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር አቶ መላኩ አለበል ተናገሩ።

የ2016 በጀት ዓመት የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል የኢንዱስትሪ ዘርፉ በ10 ነጥብ 1 በመቶ  እድገት መጨመሩን ገልጸው፥ የ7 ነጥብ 9 በመቶ ሀገራዊ የኢኮኖሚ እድገትን ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከታታይ የተተገበረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ለዘርፉ መነቃቃት ትልቅ ሚና መጫወቱንም ገልጸዋል።

በዘርፉ አዳዲስ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ባለፉት አስር ወራት 129  ከፍተኛ ኢንዱስትሪዎች ወደ ስራ መግባታቸውን  ነው ያብራሩት።

በተለያዩ ምክንያቶች ስራ አቁመው የነበሩ ኢንዱስትሪዎች በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ወደ ስራ እንዲገቡ እና የማምረት አቅማቸው እንዲያደግ መደረጉንም አንስተዋል።

በተጨማሪም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡ የፋብሪካ ምርቶችን ለመተካት በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል ነው ያሉት።

ለዚህም የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ ሁነኛ ሚና እንዳለው በመግለፅ፥ በበጀት ዓመቱ ያለፉት አስር ወራት  2 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ ምርት መተካት መቻሉን ይፋ አድርገዋል።

ይህ ውጤት በተሻለ መልኩ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻልም በ2017 በጀት ዓመት በኢንዱደስትሪ ዘርፉ የ12 ነጥብ 8 በመቶ እድገት ለማስመዝገብ መታቀዱን አክለዋል።

 

 

    

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም