ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ የፈጠራ ውድድርና ትዕይንት ሊካሄድ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ የፈጠራ ውድድርና ትዕይንት ሊካሄድ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦ "የባህል ጥበባት ለማህበረሰብ ትስስርና ለሀገረ መንግስት ግንባታ" በሚል መሪ ሀሳብ ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ የፈጠራ ውድድርና ትዕይንት ሊካሄድ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።
ውድድሩ በሁሉም ክልሎች ከወረዳ ጀምሮ ሲከናወን የቆየ ሲሆን ሀገር አቀፍ የማጠቃለያ ውድድሩ ከሰኔ 13-15/2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ይህን ያለው ሀገር አቀፍ የኪነ-ጥበብ እና ስነ-ጥበብ የፈጠራ ውድድርና ትዕይንቱን በተመለከተ ከመገናኛ ብዙሃን አመራሮችና ባለሙያዎች ጋር በአዳማ እያካሄደ በሚገኘው መድረክ ላይ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማሃዲ ጥበብ ለሀገር እድገት የማይተካ ሚና እንዳለው በመጥቀስ፥ በተለይ የባህል ጥበባት ለማህበረሰቡ ትስስር ያላቸው አበርክቶ ከፍተኛ ነው ብለዋል።
ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እድገትን በማሳለጥ የሀገረ መንግስት ግንባታን ለማሳካትም ቁልፍ መሳሪያ መሆናቸውን ጠቁመዋል።
ጥበብ በእድሜ፣ በዘርና በቀለም ሳይወሰን ከሀገር እስከ ዓለም አቀፋዊ አንድነትን የሚያመጣ ትልቅ አቅም መሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም ማህበረሰቡ ዘወትራዊ ህይወቱና የአኗኗር እሴቱ በጥበብ የተሞላ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህም ለሀገራዊ ትልሞች መሳካት መልካም እድል ነው ብለዋል።
ሆኖም ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ዛሬ ላይ የደረሰውን ይህን የኢትዮጵያ የባህል ሀብት ቱባነቱን ሊያሳጡና ሊያዳክሙ የሚችሉ ስጋቶች እየተስተዋሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
በመሆኑም የባህል ጥበባትን ከተደቀነባቸው ስጋት ነጻ ለማድረግና አጎልብቶ ለሀገር ጥቅም ለማዋል እንዲሁም ለትውልድ ለማሻገር የሁሉንም ጥረት እንደሚጠይቅ አንስተዋል።
የኪነ-ጥበብ ውድድሮችም የባህል ጥበባትን ይዘት ጠብቆ ለማቆየት ትልቅ ሚና እንዳላቸው ነው ያስረዱት።