ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ተረጅነትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የተሰሩ ስኬታማ የልማት ስራዎች ማሳያ ናቸው - ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በታታሪ ህዝቧ የተባበረ ጥረትና በመንግስት ቁርጠኝነት ከተረጂነት በመውጣት ብልጽግናዋን በአጭር ጊዜ እንደምታረጋግጥ ከለውጡ ወዲህ የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውን ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ገለጹ።

በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰሞኑን በተካሄዱ ህዝባዊ ውይይቶችም ምርታማነትን በማሳደግ የሀገርን ክብርና ሉዓላዊነት የተሟላ የማድረግ የቁጭት ስሜት ተፈጥሯል ነው ያሉት።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፣ የግብርና ሚኒስትር ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) እና የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ከኢዜአ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

በቆይታቸውም በሀገር አቀፍ የውይይት መድረኮች በተረጅነት ዙሪያ የተነሱ ሃሳቦችን፣ የተገኙ ውጤቶችን፣ የልማት ስራዎችንና የሰላምና ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተ አብራርተዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ፣ በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱ የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተረጅነትና ልመናን ባህል አድርገውት ቀጥለዋል ብለዋል።

ለችግሮች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል ሀገራዊ አቅም አለመፈጠሩ ደግሞ ለተረጅነት ስነልቦና ልምምድ አስተዋጽኦ አድርጓል ነው ያሉት።

በመሆኑም በለውጡ ዓመታት ከተረጅነት ስነ ልቦና በመውጣት በራስ አቅም አደጋን መቋቋም የሚያስችል ጠንካራ ቁመና ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር)፤ በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ፣ የተፈጥሮ አደጋና የግጭት አዙሪቶች ዕርዳታን ለመጠበቅ ዋነኛ ምክንያት ሆነው መቆየታቸውን አንስተዋል።

እርዳታን ማቅረብ የተሻለ አመራር ሰጪነት ተደርጎ መወሰዱም ለተረጂነት አስተሳሰብ ማደግ የራሱን ሚና መጫወቱን ገልጸዋል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያን ጸጋ በማልማት ጥቅም ላይ ማዋል ባለመቻሉ ተረጅነትና ልመና ልምድ ሆኖ ቀጥሏል ብለዋል።


 

ይህም የብዙዎችን የመፍጠርና የመስራት ባህል እየጎዳ መሆኑን አንስተዋል።

በመሆኑም ብልፅግና ፓርቲ በሁሉም ለሁሉም እና የሁሉም የሆነች ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው ብለዋል።

በለውጡ ዓመታትም የዜጎችን ክብር ለማረጋገጥ ፖሊሲዎቿን በነጻነት የምትተገብር ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ትምህርት የሰጡ የልማት ስኬቶች መመዝገባቸውን ሚኒስትሮቹ ገልጸዋል። 

መንግስት ተረጅነትን የማስቀረት ፖለቲካዊ ቁርጠኝነቱን ከማሳየት ባለፈ ህዝብን አስተባብሮ ፈጣን ልማትን ለማስቀጠል እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ለዚህም በሀገር አቀፍ ደረጃ የተካሄዱ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች የተረጅነት ባህልን ለመቅረፍ መግባባት፣ ወስኖና አቅዶ መተግበር የሚያስችል ተግባቦት የተፈጠረባቸው ናቸው ብለዋል።

በመድረኮቹም የነፃነት ተምሳሌት የሆነች ኢትዮጵያን ክብርና ሉዓላዊነት እየተገዳደረ የሚገኘውን ተረጂነት ለማሸነፍ መነሳሳትና መግባባት መፈጠሩን ገልጸዋል።

አመራሩና ህዝቡ የተጀመሩ የልማት ስኬቶችን በተጠናከረ መልኩ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ከመግባባት ባለፈ የቁጭት መንፈስን ፈጥረዋል ነው ያሉት።

በመድረኮቹ ላይ የተሰጠው የአመራር ስብጥር ስምሪት አንዱ ከአንዱ ልምድና ትምህርት በመውሰድ ለተሻለ የልማት ስኬት ተነሳሽነት የፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል።

ህብረተሰቡም ለተሟላ የኢኮኖሚ ነፃነት ቁጭትና ተነሳሽነት የተፈጠረበት ግንዛቤ ወስዷል ብለዋል።

የተረጅነት እሳቤን በመስበር በጀግኖች ልጆቿ ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያን የተሟላ ኢኮኖሚያዊ ነፃነት እንደምትጎናጸፍ ከለውጡ ወዲህ በአረንጓዴ አሻራ፣ በሌማት ትሩፋትና በበጋ መስኖ ህዝብን በማስተባበር የተመዘገቡ የልማት ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ፖሊሲን በመከለስ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚል ቁርጠኝነት መውሰዱንም ተናግረዋል።

አጋር አካላት ሁልጊዜ እጃቸውን ለዕለት ደራሽ እርዳታ ሳይሆን ለዘላቂ ልማት እገዛ መዘርጋት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት ሚኒስትሮቹ።

ለዜጎች ሁለንተናዊ እንቅስቃሴም ሰላምና ልማት የማይነጣጠሉ ጉዳዮች በመሆናቸው ሀገራዊ ሰላምን አስጠብቆ ብሔራዊ አንድነትና ክብሯ የተጠበቀች ኢትዮጵያን ማስቀጠል እንደሚጠበቅም አስገንዝበዋል።

ባሳለፈነው ሳምንት በሀገር አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች "ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብር እና ሉዓላዊነት" በሚል መሪ ሃሳብ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች መካሄዳቸው የሚታወስ ነው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም