ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 6/2016 (ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና ገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርመዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዳማና ሞጆ ከተሞች መካከል በ24 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፈውን  የገዳ ልዩ ኢኮኖሚ ዞን ግንባታ ግንቦት 2/2016 ዓ.ም ማስጀመራቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘለቀ ተመስገን (ዶ/ር) በስምምነት ስነስርዓቱ ላይ እንዳሉት፥ ኮሚሽኑ በኢትዮጵያ ያሉትን የኢንቨስትመንት አማራጮች በማስተዋወቅ ሰፊ ስራ እየሰራ ነው። 


 

በተለይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን በመሳብ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ወደ ትግበራ እያስገባ ነው ብለዋል።

ባለሀብቶች በኢንዱስትሪ ፓርኮች በልዩ ልዩ መስኮች ወደ ምርት እንዲገቡ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት የአገሪቷን ኢኮኖሚ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ትኩረት መስጠቱንም ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በቅርቡ የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አዋጅ ወጥቶ ወደ ስራ እዲገባ ያደረገ ሲሆን ከገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ጋር የተደረሰው "የልዩ ኢኮኖሚ ዞን አልሚነት" ስምምነትም አዋጁን መሰረት ያደረገ ስለመሆኑ አስረድተዋል።

የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለማነቃቃትና የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ  ሰፊ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የገዳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሞቱማ ተመስገን በበኩላቸው፥ የኢኮኖሚ ዞኑ ኢትዮጵያን የአፍሪካ የኢኮኖሚ ማዕከል ለማድረግ ጭምር የተመሰረተ ነው ብለዋል። 

የኢኮኖሚ ዞኑ በውስጡ የኢንዱስትሪ ፓርክ፣ የወጪና ገቢ ንግድ ማዕከል የመንገድ ግንባታ፣ የሪል ስቴት፣ የኃይል አቅርቦትና ሌሎችም ግዙፍ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች የሚያካትት መሆኑ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም