የድሬዳዋን ደረቅ ወደብና ተርሚናል የስራ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልጥ ኮንኮሪት አስፋልት መንገድ ተመረቀ - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋን ደረቅ ወደብና ተርሚናል የስራ እንቅስቃሴዎች የሚያሳልጥ ኮንኮሪት አስፋልት መንገድ ተመረቀ
ድሬዳዋ፣ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፡- የድሬዳዋ ደረቅ ወደብና ተርሚናል የስራ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳልጥና በስምንት ሚሊዬን ዶላር ወጪ የተገነባው የኮንክሪት አስፋልት መንገድ ዛሬ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት ጀመረ።
መንገዱን መርቀው ስራ ያስጀመሩት የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ምክትል ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ምህረት አብ ተክሉን ጨምሮ ሌሎች የሎጅስቲክሱ እና የድሬዳዋ አስተዳደር የአመራር አባላት ናቸው።
በምረቃው ላይ የተገኙት የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ የኮርፖሬት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ አቶ ደምሰው በንቲ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ የኮንክሪት አስፋልት መንገዱ የደረቅ ወደቡን ከዋና መንገድ ጋር በማገናኘት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።
አንድ ነጥብ ሁለት ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውና በስምንት ሚሊዬን ዶላር የተገነባው መንገዱ ወደ ድሬዳዋ ወደብና ተርሚናል የሚመላለሱትን ከባድ ተሸከርካሪዎች ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።
መንገዱ የወደቡን ሁለንተናዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያሳድግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ጠቅላላ የሎጅስቲክስ እንቅስቃሴዎችንም ፈጣንና ቀልጣፋ ማድረግ ያስችላል ብለዋል።
የደረቅ ወደቡና ተርሚናሉ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከከተማው ጋር ያለውን ትስስር በማጠናከር የህዝብን ማህበራዊ እና ምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴዎች እንደሚያሳደግም አቶ ደምሰው ገልጸዋል።
በመንገዱ ስራ ላይ ወጣቶች ጊዜያዊ የስራ ዕድል በማግኘት ለቀጣይ ህይወታቸው የሚጠቅሙ የስራ ልምድ መቅሰማቸውንም አስረድተዋል።
የኮንክሪት አስፋልቱ መገንባቱ ቀደም ሲል በጠጠራማና ኮሮንኮች መንገድ ወደ ወደብና ተርሚናል ሲገቡ በመኪኖቻቸው ላይ ሲደርሱ የነበሩ ችግሮችን እንደሚፈታላቸው የገለፁት ደግሞ የከባድ መኪና አሽከርካሪው አቶ መሐመድ ኢብራሂም ናቸው።
መንገዱ የስራ እንቅስቃሴያቸውን እንደሚያፋጥነውም ገልጸዋል።
የኮንክሪት አስፋልት መንገዱን የገነባው የቻይናው ሲቪል ኢንጂነሪንግ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን መሆኑም ታውቋል።