ቀጥታ፡

የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ፍትሃዊና ሚዛናዊ ለማድረግ እየተሰራ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ሃይል ተደራሽነትን ፍትሃዊና ሚዛናዊ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን ገለጸ።

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የኤሌክትሪክ ታሪፍ ማሻሻያን በተመለከተ ከሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አመራርና ባለሙያዎች ጋር በአዲስ አበባ ውይይት እያደረገ ነው። 

የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን በፌዴራል መንግስት የስራ አስፈፃሚ አካላት መልሶ ማቋቋሚያ አዋጅ 1263/2013 እና የነዳጅና ኢነርጂ ባለስልጣን የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ 521/2015 ከተሰጡት ኃላፊነቶች መካከል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት፣ የማስተላለፊያ፣ ስርጭትና ሽያጭን መቆጣጠር ነው። 

በባለስልጣኑ ማቋቋሚያ ደንብ አንቀፅ 5 መሰረትም ባለስልጣኑ ኃይል ለማመንጨትና ለማሰራጨት የተሰጣቸው ባለፍቃድ መስሪያ ቤቶች ያቀረቡትን የብሔራዊ ግሪድ ታሪፍ ገምግሞ የውሳኔ ሃሳቡን ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቅርቦ ያጸድቃል። 

በዚህም መሰረት የኤሌክትሪክ ተደራሽነት ፍትሃዊና ሚዛናዊ በሆነ አግባብ እንዲፈፀም የማድረግ ኃላፊነቱን ለመወጣት እየሰራ መሆኑን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ሳህረላ አብዱላሂ ገልጸዋል።

የኤሌክትሪክ ታሪፍ በ2014 ዓ.ም መጠናቀቁን ተከትሎ ላለፉት ሁለት አመታት ያለማሻሻያ መቆየቱም የኃይል አቅራቢውን ለኪሳራ እየዳረገ መሆኑንም አንስተዋል።

የከተሞች ማደግና መስፋት እንዲሁም የኢንዱስትሪዎች ቁጥር መጨመርም የሃይል ፍላጎትን ከፍተኛ አድርጎታል ነው ያሉት።

በመሆኑም የኃይል አቅርቦት አማራጮችን በማስፋት ፍትሃዊና ሚዛናዊ የኤሌክትሪክ ተደራሽነትን እውን ማድረግ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም