ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ይጀመራል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ወደ ውድድር ይመለሳል።

የሊጉ መሪ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከባህር ዳር ከተማ ከቀኑ 9 ሰዓት በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም ይጫወታሉ።

በአሰልጣኝ በጸሎት ልዑልሰገድ የሚመራው ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሊጉ ባደረጋቸው ያለፉት 5 ተከታታይ ጨዋታዎች 4ቱን ሲያሸንፍ 1 ጊዜ አቻ ወጥቷል።

በነዚህ 5 ጨዋታዎች 11 ግቦችን ከመረብ ላይ ሲያሳርፍ 3 ግቦች ተቆጥሮበታል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በ56 ነጥብ በሊጉ 1ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

ተጋጣሚው ባህር ዳር ከተማ ባለፉት 5 የሊጉ ጨዋታዎች ሽንፈት አላስተናገደም። 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ አቻ ወጥቷል። በ5ቱ ጨዋታዎች 5 ግቦችን ሲያስቆጥር ያስተናገደው 1 ጎል ብቻ ነው።

በደግአረገ ይግዛው የሚሰለጥነው ባህር ዳር ከተማ በ45 ነጥብ 3ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2 ለ 1 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

በሌላኛው የ27ኛ ሳምንት ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።

ወልቂጤ ከተማ ያለፉትን 5 የሊግ ጨዋታዎች ተሸንፏል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 3 ግቦችን ሲያስቆጥር 11 ጎሎች ተቆጥረውበታል።

በሙሉጌታ ምህረት የሚሰለጥነው ወልቂጤ ከተማ በ16 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።

ተጋጣሚው ኢትዮጵያ ቡና በበኩሉ ካለፉት 5 የሊግ ጨዋታዎች 3 ጊዜ ሲያሸንፍ 2 ጊዜ ነጥብ ተጋርቷል። በነዚህ 5 ጨዋታዎች 13 ግቦችን ሲያስቆጥር 6 ግቦችን አስተናግዷል። 

በአሰልጣኝ ነጻነት ክብሬ የሚሰለጥነው ኢትዮጵያ ቡና በ44 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ሁለቱ ክለቦች በመጀመሪያው ዙር ባደረጉት የሊጉ ጨዋታ ኢትዮጵያ ቡና 1 ለ 0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

የ27ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ነገም ቀጥሎ ሲውል ፋሲል ከነማ በሊጉ 2ኛ ደረጃ ላይ ከሚገኘው መቻል ከቀኑ 9 ሰዓት፤ ድሬዳዋ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ከምሽቱ 12 ሰዓት ላይ ይጫወታሉ።

የ27ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እስከ ሰኔ 9 ቀን 2016 ዓ.ም ይቆያሉ።

የሊጉን ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ኤርትራዊው የሃዋሳ ከተማ አጥቂ አሊ ሱሌማን በ16 ግቦች ይመራል። 

የመቻሉ ምንይሉ ወንድሙ በ13 እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሱ አማኑኤል ኤርቦና የባህር ዳር ከተማው ቸርነት ጉግሳ በተመሳሳይ 11 ግቦች ይከተላሉ።

የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከ27ኛ እስከ 30ኛ ሳምንት ጨዋታዎች በሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም እንደሚካሄዱ የሊጉ አክሲዮን ማህበር መግለጹ ይታወቃል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም