ሐረርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል - ኢዜአ አማርኛ
ሐረርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል
ሐረር ፤ ሰኔ 6/2016(ኢዜአ)፦ሐረርን ለነዋሪዎቿ እና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ የፕሮጀክት ግንባታ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን የከተማው ማዘጋጃ ቤት ገለፀ።
በከተማው የሚገነቡ የመሰረተ ልማትና የኮሪደር ልማት ስራዎች ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ እያሻገረና የስራ እድል እየፈጠረ መሆኑን የገለጹት ደግሞ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ ነዋሪዎች ናቸው።
የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ስራ አስኪያጅ አቶ ኤልያስ ዮኒስ ለኢዜአ እንደገለጹት ሐረርን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ውብ፣ ጽዱና ተመራጭ የማድረግ ስራ በከተማው በተለያዩ ስፍራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።
በተለይ በከተማው ፈርሰው በአዲስ እየተገነቡ እና እየታደሱ የሚገኙ የልማት ስራዎችን ለአብነት አንስተዋል።
በከተማው የኮሪደር ልማትም እስከ 30 ሜትር ስፋት ያለው የአስፓልት መንገድ ግንባታም እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመው የግንባታ ስራዎቹም እየተፋጠኑ መሆኑን አመልክተዋል።
ከጽዳት ጋር በተያያዘም በቀን ሶስት ጊዜ የደረቅ ቆሻሻን በማንሳት ከተማዋን ጽዱ የማድረግ ሰራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተዋል።
"ነዋሪውና ጎብኚው ወጣ ብሎ የሚናፈስበት፣ አየር የሚወስድበትና ሻይ ቡና እያለ መጽሃፍ የሚያነብበት ስፍራ ያስፈልጋል" ያሉት አቶ ኤልያስ፤ ለዚህም በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ አበረታች ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በከተማው በህገ ወጥ ንግድና በሌሎች ተግባራት የተያዙና ህብረተሰቡንም ለተለያዩ ችግሮች ሲዳርጉ የነበሩ የእግረኛ መንገዶች ባለፉት ሶስት ወራት የማስከፈትና የማልማት ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉንም ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት የሚያከናውነው የልማት ስራ ነዋሪውንና ጎብኚውን የሚያረካና ከተማዋን ወደ ተሻለ ደረጃ እየለወጠ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተሾመ አሰፋ እንዳሉት ቀደም ሲል ያልለሙ ቦታዎች አሁን በተሻለ ለምተው ለነዋሪውም ለእንግዳም ሳቢ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የክልሉ መንግስት ዘንድሮ የጀመረው የልማት ስራ እጅግ የሚያበረታታና ህዝቡንም ያስደሰተ መሆኑን የተናገረው ወጣት ጀማል አብዲረዛቅ ነው።
በአጭር ጊዜ ውስጥ ውብ ሐረርን እንደሚመለከት የተናገረው ወጣት ጀማል፤ መሰል ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።
አቶ ዳንኤል ገለቶ በበኩላቸው በከተማው የፕሮጀክት ስራ በሞያቸው የስራ እድል ማግኘታቸውን ተናግረዋል።