ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል ሥራውን ሊያጠናክር ይገባል - ቋሚ ኮሚቴው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ዘመናዊ አሠራሮችን ተግባራዊ በማድረግ አደጋን አስቀድሞ የመከላከል ሥራውን ሊያጠናክር እንደሚገባ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አሳሰበ።

ቋሚ ኮሚቴው የኮሚሽኑን የሥራ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የመስክ ምልከታ አካሂዷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት ኮሚሽኑ የጀመራቸው የለውጥ ሥራዎች፣ አደረጃጀትን የማጠናከርና በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ የጀመራቸውን ጥረቶች ጎብኝቷል።

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የተለያዩ ጥያቄዎችን አቅርበው በኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊዎች ምላሽና ማብራሪያ የተሰጣቸው ሲሆን፤ ሰፊ ውይይትም ተካሂዶባቸዋል።

ኮሚሽኑ ዘመናዊ አሠራርን በመከተል ምን ደረጃ ላይ እንዳለ፤ ተፈናቃዮችን መልሶ በማቋቋምና ወደ ቀያቸው ከመመለስ ጋር እንዲሁም ከመጋዘን ግንባታና እድሳት በተያያዘ አባላቱ ጥያቄዎችን አንስተው ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል።


 

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ዲማ ኖጎ(ዶ/ር) በዚሁ ጊዜ እንደገለጹት፤ የሚከሰቱ አደጋዎችን አስቀድሞ ለመከላከል ኮሚሽኑ የጀመራቸው ሥራዎች አበረታች ናቸው።

ይሁንና አደጋን የመከላከል ሥራውን ይበልጥ ለማጠናከርና ውጤታማ ለማድረግ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም ላይ የበለጠ መሥራት እንደሚገባም ገልፀዋል።

አደጋን ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመከላከል ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ጠንካራ ትስስር ሊኖረው እንደሚገባ ተናግረዋል።

ተፈናቃዮችን ከመመለስ ጋር በተያያዘም አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

ቋሚ ኮሚቴው ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት ግባቸውን እንዲመቱ የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

የኢትዮጵያ አደጋ ሥጋት አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማሪያም(ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፤ ኮሚሽኑ የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ በማድረግ በሂደት ከጥገኝነት መላቀቅ የሚያስችሉ አሠራሮችን እየዘረጋ ነው።


 

የለውጥ ሥራዎችን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችል ፖሊሲ ተዘጋጅቶ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ወደ ሥራ ተገብቷል ነው ያሉት።

አዳዲስ መጋዘኖችን መገንባትና ማደስ ትኩረት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ መሆኑን ጠቁመው፤ ቀብሪ ደሀር፣ ሆሳዕና እና ፍኖተ-ሰላም ከተሞች ላይ የተጀመረው ግንባታ ሥራን በማሳያነት ጠቅሰዋል።

ኮሚሽኑ በ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር ወጪ በአዳማ፣ ድሬዳዋና ኮምቦልቻ በመጀመሪያው ምዕራፍ የመጋዘን እድሳት ለማከናወን ከተቋማት ጋር ሥምምነት ደርሶ ወደ ሥራ መገባቱንም አብራርተዋል።

ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው የመመለስ ሥራውም ጎን ለጎን እየተካሄደ መሆኑን ገልጸው፤ ኮሚሽኑ ከክልሎች ጋር በመቀናጀት እየሰራ መሆኑንም አስረድተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም