ቀጥታ፡

ለስፖርተኞች ምልመላና ሥልጠና የሚያግዝ  የስፖርት ምርምር ቤተ-ሙከራ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ገብቷል - የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ

 አዲስ አበባ፤ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ የስፖርተኞች ምልመላና ሥልጠናን በቴክኖሎጂ የተደገፈ እንዲሆን የሚያደርግ የስፖርት ምርምር ቤተ-ሙከራ በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ መግባቱን የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ገለጸ። 

ዘጠነኛው አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ ዛሬ በቢሾፍቱ ከተማ ተካሂዷል።

ጉባዔው የተካሄደው "ከቤተ-ሙከራ እስከ ስፖርት ሜዳዎች፤ አብዮታዊ ለውጥ በስፖርቱ ላይ በጥናትና ምርምር ማምጣት" በሚል መሪ ኃሳብ ነው።

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው፤ መንግሥት ለአካዳሚው ከሰጠው ተልዕኮ መካከል የጥናትና ምርምር ማማከር ሥራዎች እንደሚገኝበት ገልፀዋል።

በዚህም አካዳሚው በራሱና በተጋባዥ ባለሙያዎች የኢትዮጵያ ስፖርት ላለበት ተግዳሮቶች መፍትሔ ጠቋሚ የሆነ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን እያሠራጨ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አካዳሚው ከጥናትና ምርምሩ በተጨማሪ የስፖርተኞች ምልመላና ሥልጠና ሳይንሳዊ ሂደቱን የጠበቀ እንዲሆን የሚያስችል የስፖርት ምርምር ቤተ-ሙከራ በተያዘው ዓመት በሙሉ አቅሙ ወደ ሥራ ማስገባቱን ጠቁመዋል።

ቤተ-ሙከራው አስፈላጊው መሳሪያዎችና የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ተሟልተውለት ሥራ መጀመሩን ጠቅሰው፤  ለስፖርተኞች አካላዊ፣ የጤንነት፣ የብቃትና የሥነ-ልቦና ምርመራዎች እንዲሁም ለብሔራዊ ቡድኖች የቅድመ ምርመራ አገልግሎት እየሰጠ ነው ብለዋል።

አካዳሚው የ3 ሺህ ሜትር መሰናክልና የ5 ሺህ ሜትር የክህሎት ልየታና የልማት ሥርዓት መመዘኛ ሰነድ አዘጋጅቶ ዛሬ ወደ ሥራ ማስገባቱን ጠቁመዋል።

መመዘኛው አትሌቶች ሳይንሳዊና ፕሮፌሽናል መንገድን በተከተለ መልኩ እንዲመለመሉ አስተዋጽዖ እንዳለው ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር በሌሎች ስፖርቶችም ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።


 

የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አንገብጋቢና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።

የጥናት ግኝቶች የስፖርት ኢንዱስትሪውን ፍላጎት ያማከለ፣ የባለድርሻ አካላትን አሳታፊ የሆነና የምርምር ውጤቶቹን ለፖሊሲ አስፈጻሚዎችና ባለድርሻ አካላት ተደራሽ የማድረግ ስልት መቀየስ እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።


 

የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናት፣ ምርምርና የማማከር አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር  አመንሲሳ ከበደ (ዶ/ር) አካዳሚው በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ጥናቶቹ የስፖርቱን ዘርፍ ለማሳደግ አስተዋጽዖ እንዳላቸው ገልፀዋል።

የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ የስፖርት ምርምር ጆርናሎች በማሳተም አካዳሚው ተደራሽነቱንና አቅሙን ለማሳደግና የምርምር ባለሙያዎችን ለማፍራት እየሰራ ነው ብለዋል።


 

የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ኤሊት ኢንስትራክተርና የዓለም አቀፉ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) የቴክኒክ ባለሙያ አብርሃም መብራቱ፤ የኢትዮጵያን ስፖርት እድገት ወደፊት ለማራመድ በስፖርት ሳይንሱ የሚደረጉ የጥናትና ምርምር ውጤቶችን ሥራ ላይ ማዋል ወሳኝ ነው ብሏል። 

የጥናትና ምርምር ውጤቶችን የሚለካ የግምገማ ሥርዓትና የምልመላ መስፈርቶች በሚፈለገው መልኩ አለመሟላት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ላይ አዝጋሚ ለውጥ መኖሩ የስፖርቱ እድገት ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቅሷል።

ኢንስትራክተር አብርሃም የሌሎች አገራትን ተሞክሮ በማንሳት ጥቂት ጥናቶችን በማድረግ ብዙ ሥራ በመሥራት ለውጥ መፍጠር እንደሚቻል ተናግሯል።

ለዚህም የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ተቀራርበው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክቷል።

በዛሬውም ጉባዔው የሰውነት ክፍሎች ተግባራትና የሰውነት እንቅስቃሴ፣ የስፖርት ስነ-ልቦና፣ የስፖርተኞች አመጋገብ፣ የአበረታች ቅመሞችና ሌሎች ተጓዳኝ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ የጥናትና ምርምር ሥራዎች ቀርበዋል።

ከ13 ዓመት በፊት የቋቋመው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ2006 እስከ 2016 ዓ.ም መካከል 42 ጥናትና ምርምሮችን በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ማካሄዱ በጉባዔው ወቅት ተገልጿል።

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም