ቀጥታ፡

የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅት ማድረጉን አስታወቀ

ባህር ዳር ፤ ሰኔ 5/2016 (ኢዜአ፡- የአማራ ክልል ስራና ስልጠና ቢሮ ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ፣ ጊዜ ቆጣቢና ፍትሀዊ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጥ የዲጂታል አሰራር ተግባራዊ ለማድረግ መዘጋጀቱን አስታወቀ።

ቢሮው  ከወረቀት ንክኪ ነጻ የሆነ አገልግሎት ለማስጀመር የሚያስችል በዲጂታላይዜሽን ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ የስልጠና መድረክ በባህር ዳር ከተማ  ዛሬ አስጀምሯል።

የክልሉ ስራና ስልጠና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ አማረ ዓለሙ በመድረኩ ላይ እንደገለጹት፤ የስራ እድል ፈላጊዎችን ቁጥር በአግባቡ መዝግቦ በመያዝ፣ ፍላጎታቸውን በመለየት፣ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችን አሰራር በማዘመንና ስራዎችን ከብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ማከናወን ተገቢ ነው።

ለዚህም በዴጂታል የተደገፈ የአገልግሎት አሰጣጥን እስከ ታች ድረስ ለማስፈን የሚያስችሉ መመሪያዎችና የበለጸጉ የአሰራር ሥርዓቶች ላይ ያተኮረ  የአሰልጣኞች ስልጠና መስጠት መጀመሩን ተናግረዋል።

የሚመለከተውን ባለሙያና አመራር በማሰልጠን በመጭው ዓመት ከወረቀት ንክኪ የተላቀቀ ስራ ተግባራዊ ይደረጋል ብለዋል።

የዲጅታላይዜሽን ትግበራውም ጊዜን፣ ሃብትንና ጉልበትን በሚቆጥብ መልኩ ስራዎችን ለማቀላጠፍ የሚያስችል በመሆኑ ሰልጣኞች በትኩረት እንዲከታተሉ አሳስበዋል።


 

የደብረታቦር  ዩኒቨርሲቲ መምህር ዮናታን ምስጋን በበኩላቸው፤ ከቢሮው ጋር በመተባበር ከወረቀት ንክኪ የሆነ አገልግሎትን ተግባራዊ ለማድረግ  እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በዚህም "የስራ እድል መረጃና የትምህርት እውቅና መረጃ አስተዳደር ስርዓት" የሚባሉ "ሲስተም" ማበልጸግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

የበለጸጉው "ሲስተም" በስራ እድል ፈጠራ የሚከናወኑ ተግባራትና በኮሌጆች የሚሰጠውን ትምህርት ለማዘመን  አስተዋጾ እንዳላቸው ተናግረዋል።


 

የደብረታቦር ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ቡድን መሪ አቶ  መላኩ ተስፋው፤ በመስሪያ ቤታቸው ሲስተሙ ተግባራዊ መደረጉን ተናግረዋል።

ሲስተሙ በፈጠረው ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ችግሮችን ለማቃለልና ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

ለአራት ቀናት በሚቆየው የዲጂታላይዜሽን የአቅም ግንባታ የአሰልጣኞች ስልጠና በየደረጃው የሚገኙ የስራና ስልጠና መምሪያዎች፣ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጆችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም