በሲዳማ ክልል የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በአንድ ቀን ቆጣሪ በማስገባት አገልግሎት እየተሰጠ ነው -የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል የደንበኞችን ፍላጎት ለማሟላት በአንድ ቀን ቆጣሪ በማስገባት አገልግሎት እየተሰጠ ነው -የኢትዮጵያ አሌክትሪክ አገልግሎት
ሀዋሳ ፤ ሰኔ 5/2016 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የሲዳማ ሪጅን ለአስራ አምስት ቀና የሚቆይ "ኤሌክትሪክ ለሁሉም በአንድ ቀን" ዘመቻ ለደንበኞች ቀልጣፋ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን አስታወቀ።
በሪጅኑ የደንበኞች አገልግሎትና የሽያጭ ሃላፊ ወይዘሮ ትዝታ አስናቀ እንደገለጹት፤ ከሰኔ 1 እስከ 15 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሚቆይ “ኤሌክትሪክ ለሁሉም በአንድ ቀን” በሚል ዘመቻ ተደራሽ እያደረገ ነው።
በዚህም ደንበኞች አገልግሎቱን ለማግኘት ባመለከቱ በአንድ ቀን ውስጥ የኤሌክትሪክ ቆጣሪ በማስገባት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን ተናግረዋል።
ደንበኞች ቀደም ሲል አዲስ የኤሌክትሪክ ይግባልን ጥያቄ ሲያቀርቡ ከአምስት እስከ 11 ቀናት ይፈጅባቸው እንደነበር ገልጸዋል።
በሲዳማ ክልል በሚገኙ 15 ማዕከላት እየተሰጠ መሆኑ የተናገሩት ሃላፊዋ፤ ባለፉት ሦስት ቀናት ከ200 ለሚበልጡ ጠያቂዎች ቆጣሪ እንዲያገኙ መደረጉን ተናግረዋል።
ህብረተሰቡ በየአካባቢው የኤሌክትሪክ አገልግሎቱን ተጠቃሚ ለመሆን የሚያስፈልጉ መረጃዎችን በማሟላትና ክፍያ በመፈጸም እስከ ሰኔ 15 ቀን 2016 ዓ.ም አገልግሎቱን ማግኘት እንደሚችል ተናግረዋል።
የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑት የሀዋሳ ከተማ ኮቴ ጀቢሳ ቀበሌ ነዋሪው ቄስ በየነ በሪሶ እንዳሉት፤ አስፈላጊውን ነገር ሁሉ በማሟላት በአንድ ቀን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘት ችለዋል።
ተቋሙ የነዋሪዎችን የአገልግሎት ፍላጎት ለማሟላት እያደረገ ያለውን ተግባር እንዲያጠናክርም ጠይቀዋል።
በከተማዋ የዲኤምሲ አካባቢ ነዋሪ ወይዘሮ መሰረት መድህን በበኩላቸው፤ የኤሌትሪክ ቆጣሪ በአንድ ቀን በማስገባት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ገልጸዋል።
“በፊት በዚህ መልኩ አልነበረም። አሁን ግን በአንድ ቀን የኤሌክትሪክ አገልግሎት ማግኘቴ በጣም ደስ ብሎኛል። ይህም አገልግሎቱ ያለበትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እየፈታ መምጣቱን ያሳያል" ብለዋል።
በከተማው 01 ቀበሌ ልማት ለዕድገት የሻይ ቡና ማህበር ሰብሳቢ ወጣት አዲሱ አፈወርቅ፤ ማህበራቸው ቀደም ሲል የኤሌክትሪክ አገልግሎት ስላልነበረው ከሰል እየተጠቀሙ ለደንበኞቹቻቸው አገልግሎት ይሰጡ እንደነበር ይናገራል።
አሁን ግን የኤሌክትሪክ አገልግሎት በጠየቁ በአንድ ቀን ውሰጥ አገልግሎቱን በማግኘታችን ስራችንን ቀላልና የተቀላጠፈ አድርጎልናል ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።