ዜጎች በዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል - ኢዜአ አማርኛ
ዜጎች በዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፡- ዜጎች በዲጂታል ፋይናንስ ቴክኖሎጂ ዙሪያ ያላቸውን ግንዛቤ ለማስፋት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ገለጸ።
ሚኒስቴሩ ከሰኔ 5 እስከ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ የሚቆይ አገር አቀፍ የዲጂታል ፋይናንስ ክህሎት ማዳበሪያ ንቅናቄ ዛሬ በይፋ አስጀምሯል።
ንቅናቄውን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክና ከኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በመተባበር ማዘጋጀቱ ተገልጿል።
በመርኃ ግብሩ መክፈቻ ላይ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ይሽሩ አለማየሁ (ዶ/ር) ዲጂታል ቴክኖሎጂ የዜጎችን የዕለት ተዕለት የኑሮ እንቅስቃሴ በማቅለል ለዘመናዊ አኗኗር መጎልበት ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም አስተማማኝና ተአማኒነት ያለው የፋይናንስ ስርአት በመዘርጋት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን ያግዛል ሲሉ ጠቅሰዋል።
በማህበረሰቡ ዘንድ ዲጂታል የፋይናንስ ቴክኖሎጂን የመጠቀም ዝንባሌ እየጨመረ መምጣቱ በእጅጉ የሚበረታታና ቀጣይነት ሊኖረው የሚገባ ተግባር መሆኑንም አንስተዋል።
በመሆኑም በዘርፉ የዜጎችን ተጠቃሚነትና ተደራሽነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ነው ያስታወቁት።
በአዲስ አበባ በይፋ የተጀመረው "ዲጂታል የፋይናንስ ክህሎትን የማዳበር" ንቅናቄ ለዚሁ ተግባር አንዱና ዋነኛው ማሳያ ነው ብለዋል።
ንቅናቄው ከሰኔ 5 እስከ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ በ22 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችና በ14 የቴክኒክና ሙያ ትምህርት ተቋማት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
በተመሳሳይም በእነዚህ ቀናት በሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች ንቅናቄው እንደሚካሄድ ጨምረው ገልጸዋል።
በንቅናቄው ከ200ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የዲጂታል ፋይናንስ ክህሎትን ተደራሽ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።
በሚኒስቴሩ የዲጂታል ኢኮኖሚ መሪ ስራ አስፈጻሚ አቶ ስዩም መንገሻ በበኩላቸው እንደገለጹት ዲጂታል የፋይናንስ ቴክኖሎጂ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጉልህ አስተዋጽኦ ያበረክታል።
ንቅናቄው የዲጂታል ፋይናንስ አጠቃቀምን ለማስረዳት ብሎም ጠቀሜታውን ለማጉላት የራሱ አበርከቶ እንደሚኖረው ተገልጿል።
በተጨማሪም በዲጂታል የፋይናንስ ስርአት ዙሪያ የሚፈፀሙ መጭበርበሮችን ለማስቆምና ማህበረሰቡ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ያለውን እውቀት ለማዳበር ያግዛል ነው ያሉት።
በዚህ ንቅናቄ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና ኢትዮ-ቴሌኮም ያላቸውን ዲጂታል የፋይናንስ ስርዓት በማስተዋወቅና ተጠቃሚ ላልሆኑ ዜጎች ተደራሽነታቸውን ማስፋት ላይ እንደሚሰሩ አክለዋል።
አገር አቀፍ ንቅናቄውን በቀጣይ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ተግባራዊ የማድረግ ስራው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።