በሽብርተኝነት እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሽብርተኝነት እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ነው
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ በሽብርተኝነት እና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ያተኮረ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ እና በአሜሪካ ኤምባሲ በጋራ የተዘጋጀው ስልጠናው በሽብርተኝነትና በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ምርመራ ላይ በማተኮር በአሜሪካው የፌዴራል ምርመራ ቢሮ (FBI) አማካኝነት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ ከኤምባሲውና ከምርመራ ቢሮው ለመጡት የልዑካን ቡድን አባላት እንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል አድርገው የተሳካ የስልጠና ጊዜ እንዲኖራቸውም ተመኝተዋል፡፡
በመድረኩ ላይ በኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የኦፕሬሽን ዋና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ኢትዮጵያ ሽብርተኝነትን እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን የመመርመር ተሞክሮን አካፍለዋል፡፡
ለሦስት ቀናት በሚቆየውን ስልጠና ላይ በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኢምባሲና ከአሜሪካ ፌዴራል ምርመራ ቢሮ የተውጣጡ ተወካዮች እንዲሁም ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ ከፍተኛና መካከለኛ አመራሮችና አባሎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቢሮ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።