ቀጥታ፡

​​​​​​​የመደበኛ ደም ለጋሾችን  ቁጥር ለማሳደግ የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ ህብረተሰቡ በመደበኛነት ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያጎለብት የሚደረገውን ጥረት ሁሉም ሊያግዝ  እንደሚገባ  የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ጥሪ አቀረበ።

አገልግሎቱ ይህን ጥሪ ያስተላለፈው ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም ደም ለጋሾች ቀን አከባበር  በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሀን መግለጫ በሰጠበት ወቅት ነው።

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው  20ኛው የዓለም ደም ለጋሾች ቀን “በ20ኛው ዓመት ክብረ-በዓል፣ ደም ለጋሾቻችን እናመሰግናለን " በሚል መሪ ቃል ከሰኔ 7 እስከ ሰኔ 22 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ  በተለያዩ መርሀ ግብሮች እንደሚከናወን ገልጸዋል።

በእነዚህ ጊዚያት ከሚከናወኑ ተግባራቶች መካከል በተለያዩ ክልሎች በመንቀሳቀስ ከደም ልገሳ ጋር የተያያዙ ግንዛቤ የማስጨበጫ ስራዎችን መስራት፣ የፓናል ውይይቶች፣ የጎዳና ላይ ትሪኢቶች እንዲሁም የምስጋና መርሀ ግብር ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

በሀገሪቱ የሰውን ልጅ ህይወት ከሞትና እና ከአደጋ ለመታደግ ደማቸውን እየለገሱ ያሉ  በጎ ፈቃደኞችን ለማመስገን  ብሎም በጎ ስራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ለማስቻል በዓሉ አላማ አድርጎ የተነሳው ጉዳይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተመሳሳይ ዜጎች ስለ ደም ልገሳ ያላቸውን ገንዛቤ በሚፈለገው ደረጃ ለማጎልበትም ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የደም ማሰባሰብ ስራ ሁል ጊዜ መከናወንና ጥራቱን የጠበቀ ማድረግ የሚያስፈልግ ተግባር መሆኑን አብራርተዋል።

ይህንን ለማከናወንና በጤና ተቋማት ያለውን የደም ፍላጎት ለማሟላት መደበኛ ደም ለጋሾችን ማፍራት እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ለዚህም አገልግሎቱ ህብረተሰቡ በመደበኛነት ደም የመለገስ ባህሉን እንዲያጎለብት የተለያዩ የማበረታቻ ተግባራትን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ህብረተሰቡም ይህንን ስራ እንዲያግዝ ጠይቀዋል።

አገልግሎቱ ባለፉት 11 ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ300 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ከተቋሙ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።


 

የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት አምባሳደር የሆነው አርቲስት ይገረም ደጀኔ  በበኩሉ ስለ ደም ልገሳ ጠቀሜታ ያለን ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢሆንም ወደ ተግባር ከመግባት አንጻር ክፍተቶች አሉብን ብሏል።

ይህንን በማሻሻል በመደበኛነት ደም በመለገስ የሰውን ልጅ ጤና መመለስ የሚያስችል በጎ ተግባር ማከናወን  ይጠበቅብናል ሲል ጥሪውን አቅርቧል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም