በኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጓዳኝ ለጥራቱም ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ በተጓዳኝ ለጥራቱም ትኩረት መሰጠቱ ተገለጸ
አዳማ፤ ሰኔ 05/2016(ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል የቡና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እየተደረገ ካለው ጥረት ጎን ለጎን ጥራቱን ለማስጠበቅ ትኩረት መሰጠቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ገለጸ።
በክልሉ በሚቀጥለው ዓመት የሚመረተውን የቡና መጠን 12 ሚሊዮን ኩንታል፣ ምርታማነቱን ደግሞ በሄክታር 10 ኩንታል ለማድረስ መታቀዱም ተመላክቷል።
በክልሉ በተሻሻለው የቡና ልማትና ጥራት ፓኬጅ ላይ ከሁሉም የክልሉ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ ከ700 በላይ ባለሙያዎችና የአመራር አባላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በአዳማ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ሃላፊ አቶ ጌቱ ገመቹ በመድረኩ መክፈቻ ላይ እንደተናገሩት በክልሉ የቡና ልማት ኢንሼቲቭ ተቀርጾ ተግባራዊ እየተደረገ ነው።
በዚህም ባለፉት ሶስት ዓመታት በተሰሩት ስራዎች አማካይ የቡና ምርትና ምርታማነት በሄክታር ከነበረበት ስድስት ኩንታል በዘንድሮ ዓመት ወደ ስምንት ኩንታል ማሳደግ ተችሏል።
በቀጣዩ ዓመትም ምርትና ምርታማነቱን በሄክታር 10 ኩንታል ለማድረስ ታቅዶ ለተግባራዊነቱም ንቅናቄው በመካሄድ ላይ ነው ብለዋል።
የቡና ምርትና ምርታማነቱን ለማሳደግ ያረጁ የቡና ዛፎችን ከመጎንደል ባለፈ፣ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቡና ዝርያ ችግኞች መዘጋጀታቸውንም አቶ ጌቱ ተናግረዋል።
በጥራቱም ላይ ትኩረት በማድረግ ምርቱ በዓለም ገበያ ተወዳዳሪነቱ እንዲጨምር በትኩረት እየሰራን ነው ብለዋል ሃላፊው።
በዚህም ከችግኝ ማፍላትና ከጉድጓድ ዝግጅት ጀምሮ ተከላውና እንክብካቤው ጥራቱን ለማስጠበቅ የሚያስችል ስራ እንዲሰራ በአዲሱ በጀት ዓመት ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን አመልክተዋል።
ለዚህም ከክልሉ ጀምሮ እስከ ወረዳ ድረስ ያሉ ባለሙያዎችና አርሶ አደሩ በቡና ልማትና ጥራት ፓኬጅ ላይ በቂ ዕውቀትና ክህሎት አግኝተው ለውጤታማነቱ እንዲሰሩ መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።
በኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ የቡና ልማት፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሙሐመድሳኒ አሚን በበኩላቸው፤ በክልሉ ለመጪው ክረምት ተከላ በቂ የቡና ችግኞች መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
በተጨማሪም ያረጁ የቡና ተክሎችን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ 155 ሺህ ሄክታር ላይ የጉንደላ ሥራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በክልሉ በቡና የሚለማው መሬት 3 ነጥብ 1 ሚሊዮን ሄክታር መድረሱን የተናገሩት አቶ ሙሐመድሳኒ፤ በዚህ ክረምት ተጨማሪ 381ሺህ ሄክታር በቡና ለማልማት ዝግጅት አድርገናል ብለዋል።
በተያዘው ዓመት የተሰበሰበውን 11 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል የቡና ምርት፣ በ2017 ወደ 12 ሚሊዮን ኩንታል ለማሳደግ መታቀዱንም እንዲሁ።
ባለሙያዎቹና በየደረጃው የሚገኙ አመራር አባላት እስከ አርሶ አደሩ ድረስ በመውረድ ዕቅዱን ለማሳካት ተግተው እንዲሰሩ በዚሁ ወቅት አሳስበዋል።
ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የምዕራብ አርሲ ዞን የቡናና ቅመማ ቅመም ባለሙያ አቶ ተሾመ ባልቻ እንዳሉት በዞናቸው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቡና ምርጥ ዘር ችግኞችን ከማዘጋጀት ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል።
ሙያዊ የቡና ምርት አሰባሰብ አሰራርን በመከተል የመጪው ዓመት ዕቅዱን ለማሳካት ለጥራት ትኩረት ሰጥተን እየሰራን ነው ብለዋል።
መድረኩ በአዲሱ የቡና ልማት ፓኬጅ ላይ ተጨማሪ አቅም እንደፈጠረላቸውም ባለሙያው ተናግረዋል።