ቀጥታ፡

በቀጣይ ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የአገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ):- ዛሬን ጨምሮ በቀጣይ ስምንት ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ  የአገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።   

ኢንስቲትዩት ለኢዜአ በላከው መግለጫ፤ ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች እንደሚኖር የትንበያ መረጃዎች ያመላክታሉ ብሏል።

በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብና በመካከለኛው የአገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ዝናብ ሰጪ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ ተገልጿል።

በቀጣይ ቀናት ለክረምት ዝናብ መፈጠር አስተዋጽዖ የሚያደርጉ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ከቀን ወደ ቀን እየተስፋፋና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱም ትንበያው አሳይቷል።   

ደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና ሰሜን ምዕራብና በመካከለኛው የአገሪቱ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚጨምርም ተመላክቷል።

በሌላ በኩል የቀኑ ከፍተኛ ሙቀት በሰሜን ምስራቅ በምዕራብ የአገሪቱ ሥፍራዎች ላይ ከ32 ዲግሪ ሴልሺየስ በላይ እንደሚሆን አሃዛዊ ትንበያዎች አሳይተዋል። 

በሚቀጥሉት ሣምንታት በክረምት ዝናብ ተጠቃሚ አካባቢዎች ላይ ብዙ ቦታዎቻቸውን የሚሸፍን ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸውም ተጠቅሷል።

የሚኖረውም የእርጥበት የበልግ ተጠቃሚ በሆኑት የአገሪቱ አካባቢዎች ዘግይተው ለተዘሩና የፍሬ በመሙላት ላይ ለሚገኙ የበልግ ሰብሎች፣ ለቋሚ ተክሎችና ፍራፍሬዎች የውኃ ፍላጎት ለማሟላት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተመላክቷል። 

አስቀድመው ለሚዘሩ የመኸር ሰብሎች ዘር በወቅቱ ለመዝራትና ማሳን ለማዘጋጀት አዎንታዊ ሚና እንደሚኖረውም ተገልጿል። 

በዓባይ፣ በላይኛውና መካከለኛው ባሮ አኮቦ፣ ኦሞ ጊቤ፣ ስምጥ ሸለቆ፣ አዋሽና ተከዜ እንዲሁም በጥቂት የአፋር ደናክል ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚያገኙም ነው የጠቆመው። 

ይህም በተፋሰሶች ላይ የሚኖረው የገጸ ምድርም ሆነ የከርሰ ምድር የውኃ ኃብትን እንደሚያሻሸል ነው የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የገለጸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም