በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መሆኑን ያመላክታሉ - አቶ አደም ፋራህ - ኢዜአ አማርኛ
በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መሆኑን ያመላክታሉ - አቶ አደም ፋራህ
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ በኢኮኖሚና በሌሎች ዘርፎች የተገኙ ውጤቶች መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መሆኑን የሚያረጋግጡ መሆናቸውን በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ ገለፁ።
የበጀት ዓመቱ የመጨረሻው የ100 ቀናት የአፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።
በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ሥርዓት ማስተባበሪያ ማዕከል ኃላፊ አደም ፋራህ፤ ግምገማውን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም፤ ገዥው ፓርቲ በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለማሳካት ለሕዝብ ቃል የገባቸው ግቦች እንደነበሩት አስታውሰዋል።
በፓርቲው ማኒፌስቶ የተቀመጡ ግቦችን በተግባር ዕውን ለማድረግ የዘንድሮውን ጨምሮ በየጊዜው የአፈጻጸም ግምገማዎች እንደሚደረጉ ጠቁመው፤ በግምገማውም ቃልን በተግባር ማረጋገጥ የሚያስችሉ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልፀዋል።
ለአብነትም መንግሥት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ከአፍሪካ ግዙፍ አምስት ኢኮኖሚዎች አንዱ የማድረግ ግብን ለሕዝብ በይፋ ማሳወቁን አስታውሰው፤ ይህንንም ቃል በተግባር ማረጋገጥ መቻሉን ነው የገለጹት።
የጥቅል አገራዊ ምርትን በአጭር ጊዜ 205 ቢሊየን ዶላር በማድረስ በእጥፍ ማሳደግ መቻሉን እንዲሁም በነፍስ ወከፍ ገቢም ዕድገት መምጣቱን ጠቅሰዋል።
በግብርናው ዘርፍ ከ3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በማልማትና 100 ሚሊየን ኩንታል ምርት በመጨመር ምርታማነትን ማሳደግ ስለመቻሉ ገልፀዋል።
በኢንዱስትሪው ዘርፍ ኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄን ጨምሮ በዘርፉ በተሰሩ ሥራዎች ነባር ኢንዱስትሪዎች ወደ ሙሉ አቅማቸው እንዲሸጋገሩና አዳዲስ አልሚዎችም ወደማምረቻው ዘርፍ እንዲገቡ ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።
በቱሪዝም ዘርፍና በማዕድን ዘርፎች ያሉ ዕምቅ ጸጋዎችን የመለየትና የማልማት ሥራዎችም ትልልቅ ኩባንያዎች በዘርፉ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በማስቻል ለአገር ብልጽግና የሚበጁ ተግባራት መከናወናቸውንም አንስተዋል።
በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዘርፍም የዲጂታል ኢትዮጵያ ስትራቴጂ ግብ ለማሳካት የሚያስችሉ ሰፊ ሥራዎች መከናወናቸውን በአጠቃላይ ግምገማዎቹ ቃልን በተግባር ለማረጋገጥ ጥረቱ መቀጠሉን አመላካች መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ በኢኮኖሚውና በሌሎች ዘርፎች እንደ አገር የተገኘው እመርታ መንግሥት ቃልን በተግባር እየፈጸመ መቀጠሉን በግምገማው የተገኙ ስኬቶች ማሳያ መሆናቸውን ነው አቶ አደም የተናገሩት።
ሌላው መንግሥት በየጊዜው በሚደረጉ ሕዝባዊ ስብሰባዎች የሚነሱ የሕዝብ አንገብጋቢ ጥያቄዎችን በመለየት የመፍታት ቃል አንዱ ቁልፍ ጉዳይ እንደነበር ገልጸው፤ በዚህም ተጨባጭ ለውጦች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
ለአብነትም ዓለም አቀፍ ችግር የሆነውን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል በግብይት ሥርዓቱ ላይ በተከናወኑ ተግባራት የዋጋ ንረትን ወደ 23 በመቶ መቀነስ መቻሉን ጠቅሰዋል።
በሥራ ዕድል ፈጠራ ረገድም በተያዘው በጀት ዓመት ብቻ ለ 2 ነጥብ 7 ሚሊዮን ዜጎች አዳዲስ የሥራ ዕድል እንዲፈጠር መቻሉን አንስተዋል።