የኢትዮጵያን ስፖርት ችግሮች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያን ስፖርት ችግሮች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት መስራት ይገባል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አንገብጋቢና ውስብስብ ችግሮች የሚፈቱ ጥናትና ምርምሮች ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ገለጹ።
ዘጠነኛው አገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባኤ በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ነው።
የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ጥናትና ምርምሮች እንደ ኢትዮጵያ በማደግ ላይ የሚገኙ አገራት አስተዳደራዊ፣ መዋቅራዊና መሰረታዊ ለውጦችን በማምጣት ለአገር እድገት አስተዋጽኦ እንዳላቸው አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት ውስብስብ አስተዳደራዊና መዋቅራዊ ችግሮች እንዳሉበትና እነዚህ ችግሮች ጊዜ የማይሰጡና አንገብጋቢ ናቸው ብለዋል።
በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረጉ ያሉ ጥናትና ምርምሮች ከተግባራዊነታቸው አኳያ ውስንነቶች እንዳሉባቸው አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከ2007 ዓ.ም አንስቶ በተለያዩ አርዕስቶች እያደረጋቸው ያሉ የስፖርት ጥናትና ምርምሮች ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ያላቸው አስተዋጽኦ እጅጉን የሚበረታታ ነው ብለዋል።
አካዳሚው የኢትዮጵያ ስፖርት በወቅታዊነት የሚፈልጋቸው ዘርፈ ብዙ ችግሮች ላይ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ መፍትሔ ሰጪ ሳይንሳዊ ምክረ ሀሳቦችን ማመንጨት ላይ በትኩረት እንዲሰራ አሳስበዋል።
አካዳሚው በጥናትና ምርምር ስራዎቹ አሳታፊና ሁሉን አቀፍ ለማድረግ ከዘርፉ ተዋንያን ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል።
መንግስት የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምር ስራዎች ውጤታማነት አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እንደሚያደርግ አመልክተዋል።
ውጤታማ የስፖርት ጥናትና ምርምሮች የኢትዮጵያ ስፖርት ላይ መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት፣ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ውጤታማ ለማድረግና ስፖርትን በሕብረተሰቡ ዘንድ ባህል እንዲሆን ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።
ለጥናትና ምርምሮቹ ተግባራዊነትና ውጤታማነት የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው የስፖርት ጥናትና ምርምር ጽንሰ ሀሳባዊ እውቀትንና የተግባር ስራን የማቀራረብ አቅም ያለው ዘርፍ መሆኑን ገልጸዋል።
ጥናትና ምርምሮቹ በስፖርተኞች ብቃት ላይ ለውጥ ለማምጣት፣ የአሰለጣጠን ስርዓቶችን ለመቀየር እንዲሁም ጤናማ ሕይወትና የኑሮ ዘይቤን ለመፍጠር የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
ጉባኤው የስፖርት ምሁራንና ተመራማሪዎችን፤ ከአትሌቶች፣ አሰልጣኞችና ሌሎች የስፖርቱ ተዋንያንን ጋር ያገናኘ መድረክ መሆኑን ተናግረዋል።
ጉባኤው ሀሳብ ከመለዋወጥ ባለፈ የስፖርቱ ባለድርሻ አካላት የጋራ ትብብር በመፍጠር በስፖርቱ ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እንዲመጣ ለማድረግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አመልክተዋል።
የሚቀርቡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ተግባራዊ እንዲሆኑ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የጥናትና ምርምርና የማማከር አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አመንሲሳ ከበደ አካዳሚው በተለያዩ የስፖርት ዘርፎች ጥናትና ምርምር እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸው፤ ጥናቶቹ የስፖርቱ ዘርፍ ለማሳደግ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ገልጸዋል።
አካዳሚ የተለያዩ ቴክኖሎዎችና የሳይንስ ቤተ- ሙከራዎችን በመጠቀም ውጤታማ የምርምር ውጤቶች ለማግኘት እየሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
የጥናትና ምርምር ውጤቶችን በዓለም አቀፍ የስፖርት ምርምር ጆርናሎች በማሳተም አካዳሚው ተደራሽነቱንና አቅሙን ለማሳደግ ጥረት እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከጉባኤው ጎን ለጎን ለ3 ሺህ ሜትር መሰናክልና የ5 ሺህ ሜትር ወጣት አትሌቶች የክህሎት ልየታና ልማት አሰራር ስርዓትን የያዘ ማኑዋል ይፋ አድርጓል።
በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ ርዕሶች የተዘጋጁ ጽሁፎች በመቅረብ ላይ ይገኛል።
ጉባዔው " ከቤተ- ሙከራ እስከ ስፖርት ሜዳዎች፤ አብዮታዊ ለውጥ በስፖርቱ ላይ በጥናትና ምርምር ማምጣት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።