የዓለም ደም ለጋሾች ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ይከበራል - ኢዜአ አማርኛ
የዓለም ደም ለጋሾች ቀን በኢትዮጵያ በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ይከበራል
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ):- ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም ደም ለጋሾ ቀን ከሰኔ 7 እስከ 22 ቀን 2016 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ገለጸ።
ለ20ኛ ጊዜ የሚከበረውን የዓለም ደም ለጋሾች ቀን “በ20ኛው ዓመት ክብረ-በዓል፣ ደም ለጋሾቻችን እናመሰግናለን " በሚል መሪ ኃሳብ ነው የሚከበረው።
የኢትዮጵያ ደምና ሕብረ-ህዋስ ባንክ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አሸናፊ ታዘበው ቀኑን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፤ የዓለም ደም ለጋሾች ቀን በተለያዩ መርኃ-ግብሮች ይከበራል ብለዋል።
ይህም ደም በመለገስ የሰውን ልጅ ሕይወት ከሞት ለታደጉ በጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾችን ለማመስገንና ሕብረተሰቡ ስለ ደም ልገሳ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ መሆኑን ነው ያስረዱት።
ጎን ለጎንም አገልግሎቱ ባለፉት 11 ወራት ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች ከ300 ሺህ በላይ ዩኒት ደም መሰብሰቡን ገልጸው፤ የተሰበሰበው ደም ከፍላጎት አንጻር በቂ አለመሆኑን ጠቁመዋል።
በመሆኑም ሕብረተሰቡ ደም የመለገስ ባህሉ እንዲጎለብት ዋና ዳይሬክተሩ ጥሪ አቅርበዋል።