ከአማራ ክልል 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና ወርቅ ማዕድናት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል - ኢዜአ አማርኛ
ከአማራ ክልል 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና ወርቅ ማዕድናት ለማዕከላዊ ገበያ ቀርቧል
ባህር ዳር፣ ሰኔ 5/2016 (ኢዜአ)፡- በአማራ ክልል 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና ወርቅ ማዕድናትን በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን የክልሉ ማዕድን ሀብት ቢሮ አስታወቀ።
የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ታምራት ደምሴ ለኢዜአ እንደገለጹት ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የክልሉን የማዕድን ሃብትና ፀጋ በጥናት በመለየት በስፋት እንዲለማ እየደረገ ነው።
በዩኒቨርሲቲ የዘርፉ ምሁራን ሰፋፊ ጥናቶችን በማከናወን ባለሃብቶች እንዲሰማሩ በማድረግ የማዕድን ዘርፉ ለኢኮኖሚ እድገቱ ሚናውን እንዲወጣ የሚያግዙ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፉት ዘጠኝ ወራት በተደረገ እንቅስቃሴ 19 ሺህ 950 ኪሎ ግራም የኦፓልና የወርቅ ማዕድናትን በማምረት ለማዕከላዊ ገበያ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል።
ማዕድኑ በባህላዊ መንገድ ተመርቶ ለማእከላዊ ገበያ የቀረበ መሆኑንም አብራርተዋል።
ቢሮው ሃብት በማፈላለግ፣ ባለሃብቶችንና ወጣቶችን አደራጅቶ በማስገባትና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ በትኩረት እየሰራ እንደሆነም አስገንዝበዋል።
ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር የማዕድን ሃብትና ፀጋን ለመለየት በተደረገ ጥረት እስካሁን ከ31 ሚሊየን ካሬ ኪሎ ሜትር በላይ ቦታ የሚሸፍን የማዕድን ጥናት መካሄዱን ተናግረዋል።
በዚህም ወርቅ፣ ኦፓል፣ ሊትዮም፣ ማንጋኒዝ፣ ኒኬል፣ ሳልፈር ጨምሮ 40 የማዕድን ዓይነት መገኘቱን በጥናቱ ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል።
በቀጣይ የሀገር ውስጥና የውጭ ባለሃብቶችን በመሳብ ዘርፉን ጠንካራ የኢኮኖሚ የእድገት ምንጭ ለማድረግ የሚያስችል ስራ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በደቡብ ወሎ ዞን ደላንታ ወረዳ የዋርካዬ የከበሩ ድንጋይ ማምቻ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ደሳለኝ ሞላ በበኩላቸው፤ አባላቱ የኦፓል ማዕድንን በህጋዊ መንገድ በማምረት ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ቢሮው በቅርቡ ከባህርዳር፣ ጎንደርና ወልድያ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመተባበር በ10 ሺህ ካሬ ኪሎ ሜትር ተጨማሪ ቦታ ላይ የማዕድን ፍለጋና ልየታ ጥናት ለማካሄድ ስምምነት ላይ መድረሱን ኢዜአ መዘገቡ ይታወሳል።