የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር ለአክሱምና አካባቢው ለሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች መነቃቃትን ይፈጥራል- የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር ለአክሱምና አካባቢው ለሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች መነቃቃትን ይፈጥራል- የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች
አክሱም፣ ሰኔ 05/2016 ዓም /ኢዜአ/ የአክሱም አፄ ዮሐንስ አራተኛ አውሮፕላን ማረፊያ ተጠግኖ ዳግም ሥራ መጀመሩ ለከተማዋ ብቻ ሳይሆን በአካባቢው ለሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎች መነቃቃት ሚናው የጎላ መሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአክሱም ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።
የአክሱም አፄ ዮሐንስ አውሮፕላን ማረፊያ በፌዴራል መንግስት በተመደበ 290 ሚሊዬን ብር በጀት ግንባታው ተጠናቆ ባለፈው እሁድ ሰኔ 02 ቀን 2016 ዓ.ም ሥራ ጀምሯል።
በምረቃው ወቅትም የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ እንደገለጹት፤ የአውሮፕላን ማረፊያው በይፋ ተመርቆ ሥራ መጀመር በክልሉ የሰፈነው ሰላም ውጤት ነው።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው፤ አውሮፕላን ማረፊያው 250 ሜትር የማኮብኮቢያ ስፍራ እንዲሁም 266 መንገደኞችን በአንድ ጊዜ ማስተናገድ የሚችል ተርሚናል እንዳለው መናገራቸው ይታወሳል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች መካከል በአክሱም ከተማ በቅርፃ ቅርፅ ስራ ላይ የተሰማሩት አቶ ፊልሞን ተክኤ እንደገለፁት፤ የፌዴራል መንግስት ለአውሮፕላን ማረፊያው ግንባታ በቂ በጀት መድቦ ግንባታ በማካሄድ ተቋርጦ የቆየውን በረራ መልሶ ማስጀመሩ ሰላሙን ለማጽናት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳያል።
ስምምነቱን መሰረት አድርጎ በክልሉ የሰፈነው ሰላም በልማት ሥራ ላይ እንዲሰማሩ ማድረጉን ገልፀው፤ ህብረተሰቡ በተፈጠረው ሰላም አማካኝነት ሁል ጊዜም ስለ ልማት እንዲያስብና እንዲወያይ ማድረጉንም ነው ያመለከቱት።
የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር በአድዋ እና አክሱም አካባቢ የሚገኙ እድሜ ጠገብ የቱሪስት መስህቦችን ለመጎብኘት ለውጭም ሆነ ለሀገር ውስጥ ጎብኚዎች ዕድልን እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
የአውሮፕላን ማረፊያው ሥራ መጀመር በረራው በመቋረጡ ምክንያት ተራርቀውና ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦችን አሁን በቀላሉ ለመገናኘት ያስቻለ መሆኑን የገለፁት ደግሞ የብራና ሆቴል ስራ አስኪያጅ አቶ ዲበኩሉ ልሳነወርቅ ናቸው።
በተለይ ደግሞ ለጉብኝት የሚመጡ ቱሪስቶች ከትራንስፖርት እጦት ጋር በተያያዘ ይገጥማቸው የነበረን እንግልት፣ የጊዜ ብክነትን እና ተጨማሪ ወጪን እንደሚያስቀርላቸውም አክለዋል።
ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪ አቶ ፍፁም ገብረ እየሱስ በበኩላቸው የበረራው መጀመር በዓድዋና በአክሱም ከተሞች ተቀዛቅዞ የቆየውን ሁሉን አቀፍ የንግድና ቱሪዝም እንቅስቃሴ እንደሚያነቃቃው ተናግረዋል።
በዕደ ጥበብና ቅርፃ ቅርፅ ንግድ ላይ እንደመሰማራታቸው የበረራው መጀመር ለእርሳቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ይዞላቸው እንደሚመጣም ገልፀዋል።
ለሀገር ውስጥና ለውጭ ጎብኚዎች የተለያዩ የዕደ ጥበብ ውጤቶችን በመሸጥ ተጠቃሚ ከመሆን ባሻገር ለሌሎችም የሥራ ዕድልን እንደሚፈጥሩ እምነታቸው መሆኑንም ተናግረዋል።