ቀጥታ፡

ዘጠነኛው ሀገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ):-ዘጠነኛው ሀገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ በቢሾፍቱ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በጉባዔው ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፣ የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አንበሳው እንየው፣ የኢትዮጵያ የፀረ-አበረታች ቅመሞች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር መኮንን ይደርሳል፣ የስፖርት ምሁራንና ባለሙያዎች እንዲሁም የዘርፉ ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

ጉባዔው " ከቤተ- ሙከራ እስከ ስፖርት ሜዳዎች፤ አብዮታዊ ለውጥ በስፖርቱ ላይ በጥናትና ምርምር ማምጣት" በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ነው።

ለአንድ ቀን በሚቆየው ጉባዔ የአትሌቶች ክህሎትና ብቃት መመዘኛዎች፣ ኢትዮጵያ ከአበረታች ቅመሞች ጋር በተያያዘ የምትገኝበት ሁኔታ፣ የሰውነት እንቅስቃሴና የሰውነት ክፍሎች ተግባራት፣ ስነ-ልቦና፣ የስፖርተኞች አመጋገብና ሌሎች ተዛማጅ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጽሑፎች እንደሚቀርቡ ይጠበቃል።

ሀገር አቀፍ የስፖርት ሳይንስ ጥናትና ምርምር ጉባዔ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ አማካኝነት በየዓመቱ የሚከናወን መሆኑ ይታወቃል።

ከ13 ዓመት በፊት በ290 ሚሊዬን ብር ወጪ የተገነባው የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ከተቋቋመበት ዓላማዎች መካከል ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግና ማማከር አንዱ ነው።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም