ቀጥታ፡

ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚልከው ገንዘብ በየዓመቱ በአማካይ ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር  በላይ  እየተገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 5/2016(ኢዜአ):- ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ከሚልከው ገንዘብ / ሬሚታንስ/ ባለፉት 5 ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ከ4 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱን የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት አስታወቀ።

በተጨማሪም ዳያስፖራው ለአገራዊ ጥሪዎችና የልማት ስራዎች እያደረገ ያለው ተሳትፎ እያደገ መምጣቱን ተገልጿል።

የ2016 በጀት ዓመት ከመጠናቀቁ በፊት የመጨረሻ የሆነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ100 ቀናት ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ትናንት ተጀምሯል።

የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ(ዶ/ር) በዚሁ መድረኩ  ያለፉት 100 ቀናትና የሁለተኛው ሀገር በቀል ኢኮኖሚ አፈጻጸም እንዲሁም የ2017 በጀት ዓመት የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት አቅርበዋል።

በሪፖርታቸው በ2016 በጀት ዓመት 10 ወራት ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት ከላኩት ገንዘብ (ሬሚታንስ) 4 ነጥብ 2 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር በላይነህ አቅናው በውጭ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በሕጋዊ መንገድ ወደ አገር ቤት የሚልኩት የውጭ ምንዛሬ የተሻለ እድገት ማሳየቱን ለኢዜአ ገልጸዋል።

ባለፉት 5 የለውጥ ዓመታት በየዓመቱ በአማካይ ዳያስፖራው ከ4 እስከ 5 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እየላከ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

ከዳያስፖራው እየተገኘ ያለው ገቢ ከለውጡ በፊት ከሚገኘው የውጭ ምንዛሬ አንጻር ከፍተኛ እድገት ያለው መሆኑን ጠቅሰው እድገቱ የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግ በተከናወኑ የማሻሻያ ስራዎች የተገኘ ነው ብለዋል።

ዳያስፖራው በሕጋዊ መንገድ የሚልኩትን የገንዘብ መጠን ለማሳደግ ገንዘብ የሚልኩባቸውን አማራጮች ቀልጣፋ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ መሆኑን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

 በሌላ በኩል በ2016 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ስምንት ወራት 1 ሺህ 745 የዳያስፖራ አባላት በአገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ምንዛሬ የሂሳብ ቁጥሮችን በመክፈት ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ተቀማጭ ማድረጋቸውን ጠቁመዋል።

ዳያስፖራው በኢትዮጵያ ያለውን የኢንቨስትመንት ድርሻ ለማሳደግ በበጀት ዓመቱ 9 ወራት 17 ቢሊዮን ብር ካፒታል ላስመዘገቡ 210 የዳያስፖራ ፕሮጀክቶች በክልሎች መሬት እንዲያገኙ መደረጉን አመልክተዋል።

ከፕሮጀክቶቹ መካከል 21ዱ ወደ ስራ ገብተው ለ1 ሺህ ዜጎች የስራ እድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በዘጠኝ ወራቱ ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ከስጦታና ልዩ ልዩ ፕሮግራሞች፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጀክት እንዲሁም ለልዩ ልዩ በጎ አድራጎት ስራዎች ከዳያስፖራው ከ17 ሚሊዮን ዶላር በላይ በጥሬ ገንዘብና በአይነት ድጋፍ ማሰባሰብ መቻሉን ነው ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ያብራሩት።

የዳያስፖራው ማህበረሰብ ልዩነት ሳይገድበው በሀገሩ ሁለንተናዊ ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።

መንግስት የዳያስፖራውን ተሳትፎ ለማሳደግና ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር ከክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች እንዲሁም ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዳያስፖራው በአገራዊ ጥሪዎችና የልማት ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም