የ2017 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በጀት የህዝብን የልማት ፍላጎት መመለስ በሚያስችል መልኩ የተደለደለ ነው- አቶ አህመድ ሽዴ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ):- የ2017 ዓ.ም የፌደራል መንግስት በጀት የሀገር ዕድገትን በማስቀጠል የህዝብን የመልማት ፍላጎት መመለስ ለሚያስችሉ ዋና ዋና የኢኮኖሚ መስኮች የተደለደለ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ገለጹ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ31ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል መንግስት የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሆን የቀረበለትን መግለጫ አዳምጧል።


 

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ የፌደራል መንግስት የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት የማክሮ ኢኮኖሚን በማስተካከል ተግባራዊ የሆኑ እና በዕቅድ የተያዙ የልማት ተግባራትን ማከናወን በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።

የዋጋ ንረትን በመቆጣጠርና ምርታማነትን በማሳደግ እንዲሁም የውስጥ ዕዳ መሸፈንና የውጭ ዕዳን በመክፈል የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት በሚያስቀጥል መልኩ መዘጋጀቱን አስታውቀዋል።

የገቢና ወጪ የፊሲካል ፖሊሲ አቅጣጫዎች፣ ወቅታዊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታና ማሻሻያዎች ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

የ2017 ዓ.ም ጠቅላላ ወጪ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሆኑን ገልጸው በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከጸደቀው በጀት አንፃር የ21 ነጥብ 1 በመቶ ዕድገት አለው ብለዋል፡፡

ከዚህ የወጪ በጀት ውስጥ 451 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ፣ 283 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ለካፒታል እንዲሁም 236 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር ለክልሎች የተመደበ መሆኑን አንስተዋል፡፡

ለ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ከተመደበው ጠቅላላ በጀት ውስጥ የ187 ቢሊዮን ብር በጀት ወይም 66 ነጥብ 1 በመቶ የሚሸፍነው የካፒታል በጀት መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

በጀቱ ትኩረት ለተሰጣቸው መንገድና ትምህርት፣ ግብርናና መስኖ፣ መጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን፣ ለጤና እንዲሁም ለገጠርና ከተማ ልማታዊ ሴፍቲኔት ማስፈጸሚያ የሚውል ነው ብለዋል፡፡

በጦርነት ምክንያት የወደመውን ንብረትና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ለማቋቋም ከመንግስት ግምጃ ቤት 20 ቢሊዮን ብር ተመድቧል ነው ያሉት፡፡

የምክር ቤት አባላትም የፌደራል መንግስት በጀት በየዓመቱ የሚያሳየው ዕድገት ቀጣይነት ያለው ዕምርታዊ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ልማት እየተከናወነ መሆኑን ማሳያ ነው ብለዋል።

በሁለተኛው ምዕራፍ የሀገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ መሰረት ተግባራዊ እንዲደረግ የቀረበው የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀትም የሀገርን ዕድገት የሚያስቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።

በተለያዩ አካባቢዎች ለሚስተዋሉ ግጭቶች እልባት በመስጠት በበጀት ዓመቱ የተያዙ የመሰረተ ልማት ግንባታ ስራዎችን ማሳለጥና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ዕድገት ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር ለመሰረተ ልማት ግንባታ በተመደበው በጀት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ ከሙስናና ብልሹ አሰራር በጸዳ መልኩ ጥቅም ላይ መዋላቸውን ማረጋገጥ አለበት ብለዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ፤ በማብራሪያቸው የተመደበው በጀት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን በመቆጣጠር የኦዲት ግኝት ሲከሰት ተጠያቂነትን እናሰፍናለን ነው ያሉት፡፡

ባለበጀት መስሪያ ቤቶችም የተመደበላቸውን ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል በማድረግ የሀገርን ዕድገት የማስቀጠል ሀላፊነት አለባቸው ብለዋል፡፡

ዜጎች ለሚያነሷቸው የልማት ጥያቄዎች ምላሽ በመስጠት የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ማሳካትና ሁለንተናዊ እድገት ማረጋገጥ የሚያስችል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በ31ኛ መደበኛ ስብሰባው የፌደራል መንግስት የ2017 ዓ.ም በጀት ዓመት ረቂቅ በጀት 971 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በቀረበለት መግለጫ ላይ ተወያይቶ ለፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ መርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም