የአፍሪካ ትሬድ ማርክ ፕሮጀክት የሀገራት ሰብሳቢዎች የጋራ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሄደ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ የአፍሪካ ትሬድ ማርክ ፕሮጀክት የሀገራት ሰብሳቢዎች የጋራ መድረክ(Africa Trade Mark National Oversight Committee) ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሄደ።

የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ(ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት በዛሬው ዕለት የአፍሪካ ትሬድ ማርክ ፕሮጀክት የሀገራት ሰብሳቢዎች የጋራ መድረክን (Africa Trade Mark National Oversight Committee) በአዲስ አበባ አካሂደናል ብለዋል።

በመድረኩ ላይ የአፍሪካ የነጻ ገበያ ቀጠናን ጨምሮ የሀገራት የንግድ፣ የመሠረተ ልማትና የወደብ ትስስር ዕድገት ያለበትን ደረጃ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተውጣጡ ኃላፊዎች ጋር ተወያይተናል ነው ያሉት።

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በማካሄድ ላይ የሚገኙ ዘርፈ ብዙ የልማት እንቅስቃሴዎች ልምድ በማካፈል፤ በመሠረተ ልማት ግንባታ፣ በኢንዱስትሪ ዘርፍ፣ በትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ እንዲሁም በዲጂታላይዜሽን ዘርፍ ያሉ መነቃቃቶች ሀገራችንን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ ማዕከል ብቻ ሳትሆን የአህጉራዊ ኢኮኖሚ ትስስርም ማዕከል የሚያደርጋት መሆኑን በመድረኩ ማስረዳት ችለናል ብለዋል።

በተጨማሪም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት ጋር የሚያስተሳስሩ መሠረተ ልማቶች ግንባታ፣ የወደብ አማራጮች ማብዛት፣ ብሎም የምርቶችና አገልግሎቶች ተደራሽነትን የሚያቀላጥፉ ዓቅሞችና ሥርዓታትን የመገንባት ተልዕኳችን ከኢትዮጵያ ባሻገር የአፍሪካን ኢኮኖሚያዊ የጋራ ዕድገት ያገናዘበ መሆኑን የማስገንዘብ ዕድል አግኝተናል ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም