በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት ለመትከል ዝግጅት ተደርጓል

 አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ ልማት የቡና እና የፍራፍሬ ችግኞችን በብዛት ለመትከል ዝግጅት መደረጉን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር ገለጹ።

የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ብሔራዊ ዐቢይ ኮሚቴ እንዳስታወቀው ለ2016/17 ዓ.ም የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ7 ቢሊየን በላይ ችግኞች ዝግጁ ተደርገዋል።

ለዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በከፍተኛ ርብርብ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በቅርቡ መግለፃቸው ይታወሳል።

የተከላ ስፍራዎች ተለይተው፤ በአረንጓዴ ልማት የአካባቢ ጥበቃን ዘላቂ ለማድረግና የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በመሆኑም ለመርሃ ግብሩ መሳካት ሁሉም የማህበረሰብ ክፍሎች፣ የተለያዩ ተቋማትና ትምህርት ቤቶች ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝበዋል።

ከዚህ አንፃር በሁሉም ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች እንደ አካባቢዎቹ ነባራዊ ሁኔታ የተቀናጀ ጥረትና ዝግጅት በመደረግ ላይ መሆኑ ታውቋል።

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ኡስማን ስሩር፤ ለመርሃ ግብሩ መሳካት ሁለንተናዊ ዘግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የፍራፍሬ፣ የእንሰት፣ የሙዝ፣ የእንስሳት መኖ፣ የቡና ችግኞችን ጨምሮ ሁለገብ የኢኮኖሚ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች ለተከላ ዝግጁ ስለመሆናቸውም ጠቅሰዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ልማት የአየር ንብረት መዛባትን ከመከላከል ባለፈ የምግብ ዋስትና እና የሀገር ልማት መሰረት በመሆኑ የሁሉም የጋራ ጥረትና ትብብር አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል። 

 
 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም