የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚመጥን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ ዘርፉን የሚመጥን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር አስታወቀ።

ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስትቲዩት 11ኛውን የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት "ቱሪዝም ለሀገራዊ መግባባት "በሚል መሪ ሃሳብ በተለያዩ መርኃ ግብሮች ማክበር ጀምሯል።


 

መርኃ ግብሩ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ሲሆን በዛሬው ፕሮግራም በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የሚገኙ ማህበረሰቦች ባህላዊ ምግቦቻቸውንና መገልገያ ዕቃዎቻቸውን አቅርበዋል።

በአፋር ፣ሀረሪ ፣ሲዳማ እና ጋምቤላ ክልል የሚኖሩ ማህበረሰቦች ባህላዊ ምግቦቻቸውንና መገልገያ ቁሶቻቸውን ለዕይታ አቅርበዋል።


 

በዚሁ ወቅት የስራና ክህሎት ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ተሻለ በሬቻ በተለያዩ የስራ ዘርፎች ብቃት ያላቸውን ሙያተኞች ለማፍራት ሚኒስቴሩ ክህሎትን መነሻ ያደረገ ስራ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ኢንስቲትዩቱ ማካሄድ የጀመረው የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት በዘርፉ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራት ብሎም የሀገሪቱን ባህል ለማስተዋወቅ ያግዛል ብለዋል።

የቱሪዝም ዘርፍ አገልግሎት ላይ የተመሰረተ ቢሆንም እንደ ሀገር በዘርፉ ያለው አገልግሎት አሰጣጥ ከሌሎች አገራት ጋር ሲወዳደር ብዙ ስራዎች መስራት እንደሚጠበቅብን አመላካች ነው ብለዋል።

በሀገሪቱ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ሆቴሎች እየተስፋፉ በመሆናቸው ዘርፉ ለሀገር ተገቢውን ጠቀሜታ እንዲያስገኝ ሙያተኞች በዕውቀትና በክህሎት ብቁ እንዲሆኑ መስራት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ለዚህም ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ እየተስፋፋ ያለውን የቱሪዝምና የሆቴል ኢንዱስትሪ የሚመጥን ብቁ ባለሙያ ለማፍራት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የኢንስትቲዩቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው ነጋሽ በበኩላቸው ተቋሙ በቱሪዝም ዘርፍ ብቁ ሙያተኞችን ለማፍራትና የሀገሪቱን ባህላዊ ምግቦች በሚፈለገው ደረጃ ለማስተዋወቅ የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል፡፡


 

ለዚህ ይረዳው ዘንድ በዘርፉ ስልጠና ከመስጠት ባለፈ በጥናትና ምርምር የተደገፉ ውጤቶችን ለማውጣት የጀመራቸውን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

ኢንስቲቲዩቱ በዘርፉ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በየዓመቱ የቱሪዝምና እንግዳ ተቀባይነት ሳምንት እንደሚያካሄድ ገልጸው የዛሬው ተመሳሳይ ፕሮግራም የዚሁ አካል መሆኑን ጠቁመዋል።

ለሶስት ቀናት በሚቆየው መርኃ ግብር በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ በሚገኙ ባለሙያዎች መካከል ልዩ ልዩ የክህሎት ውድድር ፣ኤግዚቢሽንና ሲምፖዚየም መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡

በዚህም የሰልጣኖችንና የአሰልጣኞችን የሙያ ብቃት ለማሻሻል ጥረት እንደሚደረግ አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም