የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን ምስረታ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርአት ሊካሄድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፦ የክብር ዶክተር አርቲስት አሊ ቢራ ፋውንዴሽን ምስረታ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርአት ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓም በአዲስ አበባ ይካሄዳል።

የኦሮሚያ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ ደራራ ከተማ የፋውንዴሽኑን ምስረታ ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።


 

በመግለጫቸውም ፋውንዴሽኑ በሀገር ውስጥና በውጭ ከተመሠረተ አንድ ዓመት እንደሆነው አስታውሰው አሁን ላይ ለህዝብ ይፋ የማድረግ ስነ ስርአት የሚካሄድ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም መሰረት የአርቲስቱ ፋውንዴሽን ምስረታ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርአት ሰኔ 16 ቀን 2016 ዓ.ም በአዲስ አበባ የሚካሄድ መሆኑን ተናግረዋል።

በጥበብ ስራዎቹ ለሀገር ያበረከተውን አስተዋጽኦ በማውሳት ሌጋሲውንም ለማስቀጠል የፋውንዴሽኑ መቋቋም ትልቅ ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተው በክልሉ መንግስት በኩል ድጋፎች የሚደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርቲስቱን ሌጋሲ ለማስቀጠልም የሁሉም እገዛ አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰው የተጠናከረ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።

የአርቲስቱ ባለቤትና የፋውንዴሽኑ መስራች ኢሊሊ ማርቆስ ቢራ፤ የፋውንዴሽኑ አላማ አርቲስቱ በህይወት ዘመኑ ያከናወናቸውን ድንቅ ስራዎች የሀገር እሴትና የትውልዱ መማሪያ ለማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በመሆኑም በፋውንዴሽኑ ምስረታ ይፋ ማድረጊያ ስነ ስርአት ላይ ሁሉም እንዲሳተፍና ለፋውንዴሽኑ ድጋፍ በማድረግ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ጠይቀዋል።

የፕሮግራሙ አስተባባሪ ደመቀ ነጋሳ፤ ፋውንዴሽኑ ከተመሰረተ ዓመት ያስቆጠረ ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች በይፋ ወደ ስራ አለመግባቱን ገልጸዋል፡፡


 

በመሆኑም አሁን ላይ በይፋ ለህዝብ የማስተዋወቅና የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብር ለማካሄድ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም