የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በመጪው ሐምሌ ወር መጀመሪያ ይሰጣል

አዲስ አበባ ፤ ሰኔ 4/2016(ኢዜአ)፡- የዘንድሮ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በመጪው ሐምሌ ወር መጀመሪያ እንደሚሰጥ ተገለፀ። 

የትምህርት ሚኒስቴርና የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ፈተናውን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች አገልግሎት ምክትል ዳይሬክተር ተፈራ ፈይሳ በዚሁ ጊዜ እንደገለፁት፤ የዘንድሮው ዓመት 12 ክፍል ፈተና ከትግራይ ክልል ውጭ ባሉ አካባቢዎች ሐምሌ 3 ቀን 2016 ይጀመራል።

በዚህም መሠረት ከሐምሌ 3 እስከ 5 የሶሻል ሳይንስ ፈተና የሚሰጥ ሲሆን የተፈጥሮ ሳይንስ ፈተና ደግሞ ከሐምሌ 9 እስከ 11/2016 ዓ.ም እንደሚካሄድ ነው የገለፁት።

በትግራይ ክልል ደግሞ በሁለት ዙር ፈተናው የሚሰጥ ሲሆን ሐምሌ 2 ተጀምሮ ሐምሌ 12 እንደሚጠናቀቅ ጠቁመዋል።  

በትምህርት ሚኒስቴር የትምህርት ዲጂታላይዜሽንና የአይሲቲ መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዘላለም አሠፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የዘንድሮው ዓመት የ12 ክፍል ፈተና በኦንላይንና በወረቀት እንደሚሠጥ ተናግረዋል። 

በዘንድሮው ዓመት 701 ሺህ 489 ተማሪዎች የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች መኖራቸው ተገልጿል።

ትምህርታቸውን ዘግይተው የጀመሩና በተለያዩ ምክንያቶች በዚህ መርኃ ግብር መሰረተ ፈተና ላይ መቀመጥ ለማይችሉ ተማሪዎች ሁለተኛ ዙር ፈተና እንደሚዘጋጅ ጠቁመዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም